አንኳን ለሆሳዕና በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
#እርማችንን ማን ከመካከላችን ያጥፋልን?
#የቤተ መቅድሱን ወንበዴዎች፣ ሻጭ ሸቃጭ ለዋጮችን ማን ያጽዳልን?
በዓለ ሆሳዕናን ባሰብኩ ቁጥር ሦስት ጥያቄዎች (ጉዳዮች) እዕምሮዬ ላይ ይመላለሳሉ:-
1. እኛ ብቻ አናውቅላችኋለን፣ የቤተ መቅደሱ(ሙኩራቡ) ጠባቂዎች የእግዚአብሔር እና የሕጉ አክባሪ አስከባሪ ጠበቆች እኛ ብቻ ነን የሚሉ ጸሐፍት እና ፈሪሳውያን ክርስቶስን ለመቀበል፣ ከእውነት ጎን ለመቆም፤ ስለ እውነት ለመመስከር ለምን አልቻሉም ?
2. መቅደሱን መሽጫ መሸቀጫ የወንበዴዎች ዋሻ እስከማድረግ ያደረሳቸውን ድፍረት ከየት አገኙ? ከላይ የተጠቀሱት የመቅደሱ ጠበቆች፣ የሕግ አክባሪና አስክባሪዎች ነን ባዮች ለምን የመቅደሱን የጸሎት ቤትነት ማስከበር(መጠበቅ) አልቻሉም?
3. የበዓለ ሆሳዕና ድምቀት ለሆኑ ሕጻናት(ተተኪ ትውልድ) የምናወርሳቸው ምንድነው? የሚሉት ናቸው።
እነዚህን ሦስት ጥያቄዎች (ጉዳዮች) አፍታቶ ማየት ለዛሬዬቱ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የአማኞቿ የሞራል ልዕልና ማጣት፣ በማኅበራዊ ሕይወት እና በኢኮኖሚያዊ ይዞታ የበታችነት አመክንዮ ለመረዳት ከማስቻሉ በላይ ለነገዪቱ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ እድገት ለመሥራት ያነሳሳል ብለን እናምለን።
የዚህ ገጽ አባላት ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደዚህ መንደር ብቅ ብለን ለመጻፍ የተመለስነው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና የማይቀብሉ ካህናት(አገልጋዮች) እና ምዕመናን ፣ ለውጥ ፈላጊ እና ተራማጅ የሆኑ አባቶችንና የቤተክርስቲያኒቱን አገልጋዮች ላይ ያነጣጠረ የሞራል ገድላ(Character Assassination) በማድረግ የማዳክም ሥራ፤ በዕቅድ(በዓላማ) ኃላፊነት እና ሥልጣን የተሰጣቸውን የመንጋው ጠባቂዎችን ተቀባይነት ለማሳጣት ”እረኛውን ምታ በጎቹም ይበተናሉ” የሚል መርህ በመያዝ ያለ እረፍት እና ያለ መታከት አጽራረ ተዋሕዶዎች ከውስጥም ከውጪም እየሠሩ መሆኑን በመገንዘባችን ነው፡፡
እሊህ አጽራረ ተዋሕዶዎች ቤተክርስቲያናችንና መዋቅሯን ለመናድ በሚናበቡ ነገር ግን የተለያዩ በሚመስሉ ቡድኖች የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ይኸውም፡-
#የጥቅምትና የግንቦት ሲኖዶስ ስብሰባ በመጣ ቁጥር አባቶች አንድ ቦታ ተረጋግተው ከሠሩ እኩይ ተግባራቸው ስለሚነቃ እና ጥቅማቸው ስለሚቀርባቸው አጀንዳ የሚፈበርክ ቡድን፤
#ለቤተክርስቲያን መዋቅር የማይገዙ የካህናት፣ የአብያተ ክርስቲያናት፣ የአካባቢ ወጣቶች እና የምዕመናን ኅብረት በማቋቋም(በተለይ በውጪው ዓለም) ምዕመናን እና አባቶችን በጊዜያዊ አጀንዳ ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ የሚያደርግ ቡድን፤
#በአባቶች መካከል፣ በአባቶች እና ምዕመናን መካከል አለመተማመን ፣ አለመከባበር እንዲኖርና እና በአባቶቹ ተስፋ እንዲቆርጥ በማኅበራዊ ሚዲያ የሞራል ገደላ(Character Assassination) በመፈጸም ተግቶ የሚሠራ ቡድን፤
#የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን ምዕመናን ከማኅበራዊና ከፖለቲካዊ ሱታፌ እንዲሁም ከኦኮኖሚያዊ ተጽእኖ ፈጣሪነት ውጪ ማድረግን አሳክተናል ብለው ስለሚያስቡ ምዕመናን ከሱታፌ ቤተክርስቲያን(ከአገልግሎት) ውጪ ማድረግን በሰበካ ጉባኤ እና በሰ/ትቤት አመራርነት፣ በቤተክርስቲያኒ የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ መሳተፍን እንደ ኮረንቲ እንዲፈራው በማድረግ ቤተክርስቲኒቱ ሰው ያጣች ይመስል በሥነ ምግባር ጉድለት የሚታወቁና ከአንድ መደብ በወንብድና በዝርፊያ የተነሱ የራሳቸውን አባላትን በማስመደብ በየደረጃው ያለውን የሥልጣን ተዋረድ ጠቅልሎ የሚይዝ የሚያስዝ ቡድን፤
ማደራጀት ጥቂቶቹ ሲሆን ወደ ፊት እያንዳንዱን በዝርዝር የምንሄድበት ይሆናል፡፡ በዚህ መሠረት በቀጣይ ጽሑፎቻችን፡
1. የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ዛሬ ያለችበት አስተዳደራዊ እና መዋቅራዊ ልፍስፍስነት፣ ልሽቀትና ድክመት ላይ እንድትደረስ እነማን ምን ድርሻ ነበራቸው/አላቸው?
2. እነማን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን ለማድክም ብሎም ለማጥፋት በዕቅድ እየሠሩ ነው/ነበሩ?
3. ሕገ ቤተክርስቲያን ስለነማን ምን ይላል እያንዳንዳችን ድርሻችን ምን ድረስ ነው?
4. ለሚቀጥለው ትውልድ በሰፊው ተዘፍቀንበት ያለውን አባቶችን ማቃለልን፣ ማዋረድን እና የሞራል ገደላ(Character Assassination) ነው የምናስተላልፈው?
እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ላይ በመወያየት፣ ጥያቄዎችን በመመለስ ፣ አስተያየት በመስጠት እና በመቀበል የቱንም ያህል ጊዜ ቢፈጅ አጽራረ ተዋሕዶን ለማስታገስ በዓላማ በእቅድ እየሠሩብን እንዳሉ ሁሉ እኛ እንዲሁ ለመሥራት ቃል እንገባለን፡፡
#ለዛሬ ግን
እርማችንን ማን ከመካከላችን ያጥፋልን?
በእስራኤል ዘሥጋ ታሪክ ውስጥ ሙሴንና አሮንን ጨምሮ ከግብጽ የተነሣው ማርና ወተት ወደ ምታፈሰው ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲገባ ተስፋ ተስጥቶት የነበረውን #ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በምድረ በዳ መክኖ ተንከራቶ እንዲቀር እንዲሞት ያደሩጉት እና ለሽንፈት ምክንያት የሆኑት ሁለት ዋንኛ ታሪኮችና ክስተቶች በስሱ እናነሳለን፡፡
1. በኦሪ.ዘኁ 13 እና 14 ከ12ቱ ሰላዮች መካከል አሥሩ #ክፉ ወሬ በማውራት ራሳቸውንም ሆነ ሕዝቡን(600 ሺህ ሕዝብ) በበረሃ እንዲጠፋ ያደረጉበትንና
2.በ መ. ኢያ 7 እስራኤል በጋይ ሰዎች እንዲሸነፉ እና በመጨረሻ ለመላ ቤተሰቡ መሞት ምክንያት የሆነውን ያልተፈቀደ ተግባር በመፈጸም በእስራኤል መካከል እርም የሆነውን ነገር የደበቀው የዛራ ልጅ አካን ታሪክ ማየት ለወደፊት ለምናነሳቸው ጉዳዮች እጅግ ጠቃሚ ታሪኮች ናቸው፡፡
በእኛ እምነት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ዛሬ ላለችበት ደረጃ ያደረሷት እና ልጆችዋም በማያቋርጥ መጠላላት፣ መነቃቀፍ እና መጠፋፋት ውስጥ እንዲጓዙ እያደረጉ ያሉት እነዚህ ጉዳዮች ናቸው ብለን በብርቱ ስለምናም በማያቋርጥ ጥረትና ትግል በእግዚአብሔር ፈቃድ፣ በቅዱሳን ምልጃና ጸሎት ልንፈታቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል፡-
1. #ክፉ ወሬ እንደ ማውራት ማኅበራዊ ሚዲያዎቻችን ቤተክርስቲያንና አገልጋዮችን በመተቸት በማሸማቀቅ የተሙሉ በመሆናቸው
2. #እርም ነገርን እንደ ዛራ ልጅ አካን እንደ መደበቅ ነውር የሆነ ዘረኝነትን፣ የግል ጥቅምን ብቻ ማሳደድን፣ እኔ ብቻ አውቅላችኋለሁ ባይነትን እና ለመንጋው አለመጨነቅን ፣የመድረክ ብቻ(የታይታ) ክርስቲያንነት ማስወገድ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት
ከነዓን መንግሥተ ሰማያት ከመግባት እንዳያስቀረን፤ የመከነና የባከነ አማኞችን ቁጥር ቀንሶ እንደ ጌታ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚኖር ምዕመናን ለማብዛት የሚረዳን በመሆኑ እግዚአብሔር ቢያደርሰን ቢያቆየንና ቢፈቅድ ከትንሣኤ በዓል በኋላ ከላይ ያነሳናቸውን ጉዳዮች በዝርዝር እንሄድበታለን፡፡
ይቆየን
ተጻፈ መጋቢት 27 ቀን 2018 ዓ.ም፡፡