ሰላም ተወዳጆች!
ይህን ጦማር እሰከምጽፍበት ቀን ድረስ የ”ሞዐ ተዋሕዶ” የምሥረታ ዜና ድንጋጤን፣ ግርምትንና ግራ መጋባትን ፈጥሮብኝ ከመሥራች ጉባኤ ተሳታፊ እስከ ጽንፍ ተቃዋሚ ሰዎችን ሀሳብ ለመረዳት ሞከርኩ ነገር ግን አሁን ድንጋጤዬ፤ ግርምቴና ግራ መጋባቴ ቀጥሏል፡፡
ድንጋጤዬ፡- በማስተዋልና በብስለታቸው የማከብራቸውና ተስፋ የምጥልባቸው መ/ር ፋንታሁን ዋቄ፣ ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ፣ ዶ/ር ዘርዓየሁ ስሜን የመሳሰሉ ሰዎች አልፎ አልፎ በፈቃደኝነት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አሰስተወዋጽኦ ሲያደርጉ አእነንደነበረሩ በቢተታወቀቅመም በሚጠሉትና በሚኮንኑት በሆቴል መስብሰብን ተግባራዊ አድርገው ኢ-መዋቅራዊ፣ አደገኛ፣ ከፋፋይ፣ ሌላውን ያገለለ የተነናጥል የቡድንና የሸፍጥ አሠራር አሁን ግን አእነሰሱ ራሳቸው ተዘፍቀው መገኘታቸው ይገርማል! ከድጡ ወደ ማጡ ይልሃል ይሄ ነው!ሎቱ ስብሐት!
ግርምቴ፡- መድረኩን ሲመሩ የነበሩ አባቶች ጴንጤያዊ የማስፎከርና ዘመንኛና አስጨብጫቢ ቲፎዞ ፈላጊ ሰባክያን የሚጠቀሙበትን መንገድ እጅግ የተከበሩ ሰዎች በተሰበሰቡበት ጉባኤ በባዶ ፉከራ ሲያስጨበጭቡ መዋላቸው ይገርማል!፤ ለምሳሌ ይሄንን ለመረዳት ይቺን ያዳምጧት https://youtu.be/vLMPonfS5fk
ግራ መጋባቴ፡- ፍሬ አልባ ሆነው እንደመከኑ በርካታ ጥቅመኛ ማኅበራትና ግብረ ኃይሎች ስብስብ መሥራቾች እና የቤተ ክርስቲያን መጠቃትና ተቆርቋሪነት መነሻ አድርጎ፣ ብዙ ተወርቶለት፣ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ሸክም የሚጋራ ተቋም ተመሠረተልን ብለን ተስፋ አድርገን ሳለ ለመሪዎቹ(ኮሚቴዎች) ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤትና የጥቅማ ጥቅም ስጦታ እነሆ ተብሎ እንዲመክንና የቴሌቪዥን መስኮት አዳማቂ ብቻ ሆኖ እንዲቀር የሆነውን የ”ጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት” መስራቾች ዛሬ ደግሞ “ተዋሕዶ ታሸንፋለች!” ብለው በሌላ ገጽ፤ በሌላ መሠረት መምጣት ለምን ፈለጉ? መልስ የለም! ግራ መጋባቴ ቀጥሏል…
“የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት፣ በፍቅርና በመተሳሰብ ያሸንፋል!” ከማለት ይልቅ “ኢትዮጵያ ታሸንፋለች” ሲሉ ምን እያሉ እንደሆኑ የሚያውቁት አይመስለኝም፡፡ በየጊዜው የሚነሱ ተዋንያን እንድናተርፍ ያደረጉን ረሀብ፣ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ የሥነ መንግሥት የአመራር ችግር ነው፡፡ ነጻ ማውጣት የሚቻለው በልዑል እግዚአብሔር መሪነት በቃልም በሥራም እንጂየጭድ እሳት ይመስል በፍከራና በመንቦግቦግ አይደለም፡፡ ማሸነፍ የሚገኘው በጥበብ በማስተዋልና ሁሉን ተረድቶና አሳትፎ በመጓዝ ነው፡፡ታዲያ ኢትዮጵያ አሸንፋለች?
አሁንም ሁሉን አቀፍ ያልሆነ፣ኢ-መዋቅራዊና ከአባቶች ጋር መግባባትና ይሁኝታ ያላገኘ አካሄድ ይዞ ተዋሕዶ ታሸንፋለች ማለት ከድጡ ወደ ማጡ ይከተን ካልሆነ በቀር መፍትሔ ያመጣል የሚል ግምት የለኝም፡፡
ይሄንን ለማሳየት አንድ ምሳሌ ላንሳ በትግራይ ክልል የነበረውን ችግር ለመፍታት ከቱርክ ተሞክሮ ተወስዶ በዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም ተቋም ተጠንቶ በወቅቱ የነበረውን የእስላሞች እንቅስቃሴ ለማስተንፈስ ተብሎ የተቋቋመው “የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ” እና የሰላም ሚኒስቴር ማንንም ሳያማክሩ አንድ ውሳኔ ይወስናሉ፡፡ ይኸውም 95% የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኝ ባለበት ክልል የቅዱስ ሲኖዶስን አባላትን ሳያማክሩና የመፍትሔው አካል እንዲሆኑ ሳያደርጉ ቢያንስ እንኳን ዛሬ ራሳችንን ችለናል ብለው መግለጫ እስከ ማውጣት የደረሱ የትግራዋይ 4/5 ጳጳሳትን ሳያካትቱ ለሥልጣን የሚሻኮቱ የፓለቲካ ኃይሎችን ኩርፊያ ለማስማማት የተደረገው እንቅስቃሴ ተቃባይነትን ካለማግኘቱ ባሻገር አድርገናል ለማለት ያህል ለፖለቲካ ፍጆታ ዋለ እንጂ መፍትሔ እንደማያመጣ እየታወቀ የተዋቀረ ግብረ ኃይልና ስብስብ ነበር፡፡


ሞዐ ተዋሕዶ ግብረ ኃይል ከድጡ ወደ ማጡ ወሳጅ ጎዳና የሚሆነው ለምንድነው
ሀ. ማኅበሩ በርካታ የሠራቸው ፍሬያማ ሥራዎች፣ እንዲጫጩና ልክ ማደበሪያ እንደለመደ መሬት እንዲመክኑ ትልቁን ሚና ሲጫወት የቆየው በውጪ የስለላ ድርጅት ተላላኪነቱን በመጠቀም አቅም ያላቸውንና እውነተኛ የተዋሕዶ ልጆችን በማሳደድና ብፁዓን አባቶችን እንዲከፋፈሉና አንድነት እንዳይኖራቸው እንደ አይጥ በፁዓን አባቶች ቤት እየተሹለኮለካና ድብቅ ካሜራ ጭምር በማስቀመጥ ሲያተራምሰንየኖረው፤ ቀድሞ ከቁልፍ የሕወሐት ሰዎች ጋር ጥብቅ ቁርኝነት የነበረው፤ በኋላ ግን ጥቡዓን በሆኑ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁላችንም በተገኘንበት ደባውና ሴራው በማጋለጥ አንተ ሰላይ እጅህን ከቤተ ክርስቲያን ላይ አንሳ ስለተባለና ስለተነቃበት እናቱ እንሞተችበት በአንድ ጉባኤ ስቅስቅ ብሎ ያለቀሰው እና ዛሬ ደግሞ የተጋለጠውንና ያልተሳካውን ካባውን ቀይሮ የአዲሱ ፓርቲ አባል ሁኖ በልጽጎ ፓርላማ ገብቶ ያለው ባያብል ሙላቴን የመሳሰሉ መሰሪዎችና ዲቃላዎችነቀርሳዎች ከጀርባ መኖራቸው ነው፡፡


- ለ. በስልክና በትስስር መስመር ላይ ብቻ ያሉትን ብቻ ያካተተ መሆኑ ነው፡፡ ይህም ማለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዳት፣ ስደት፣ መከራ እየደረሰባት ያለው ከየትኛውም ጊዜ ይልቅ በዚህ ዘመን መሆኑ እሙን ነው፡፡ ተዋሕዶ ማሸነፍ የምትችለው በቅዱስ ሲኖዶስ ምክርና ውሳኔ፤ በሊቃውንትና በገዳማውያን ጸሎትና ግሳጼ፣ በእውነተኛ ሰባክያን መሰጠትና ትምህርት፤ በሰ/ት/ቤት ተማሪዎች አገልግሎትና ትጋት እንጂ 90% የማኅበሩ ደጋፊ በሆኑበት ግብረ ኃይል ሊሆን አይችልም፡፡
ሐ. ማሸነፍ የምንችለው ችግር በተከሰተ ቁጥር ገንዘብና እርዳታ ሰብሳቢና አሰባሳቢ በመሆንና እዚህም እዚያም ግብረ ኃያልና ማኅበር በማቋቋም ሳይሆን ሕጻናት እየተጫወቱበት ያለውን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየደረጃው ያሉ መዋቅር ውስጥ ገብቶ በማገልገልና በማጠናከር እንጂ ምንም እንኳ ጠቃሚ ሀሳብ ብንይዝም የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይና ወሳኝ አካላት ምንም አያመጡም ወይም አቅም የላቸውም በሚመስል እሳቤ ወደ ጎን በማለትና እንደ አሜባ በማባዛት አይደለም፡፡ ስማቸው ሊወድቅ ወይም ገቢያቸው ሊቀንስ ሲጀምር በድርድ ያስቀመጧትን መረጃ ብቅ እያደረጉ ወሳኝ አካላት ናቸው ብለን እንድናስብ በይሉኝታ ላም እሳት ወልዳ ዓይነት የሆኑ ያሉን ማኅበራትና ግብረ ኃይሎች ይበቁናል፡፡
መ. የሞዐ ተዋሕዶ ባለ ሰባት ነጥቡ የአቋም መግለጫ ሲጠቃለል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ራሷን የቻለች፣ ተደማጭነት ያላት፣ ማንም እንደፈለገ የማያሽከረክራት ተቋም ሁና ማየት ነው ብዬ ወስጄዋለሁ፡፡ ይህ ከሆነ ቤተ ክርስቲያን ማሸነፍ የምትችለው ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ ራሷን ስትችል እንደሆነ አምናለሁ፡፡
ነገር ግን በታሪካችን ውስጥ ይህ ጉዳይ ያልተሳካበትን መንገድ ማየቱ ለዛሬ ከጠቀመን እነሆ፡-
1ኛ. ደጃዝማች ወልደ ሰማዕት ገብረ ወልድ “ሕይወቴ” በሚለው መጽሐፋቸው ከገጽ 522-24 ላይ እንዳሠፈሩት በንጉሡ ጊዜ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ራሷን ችላ እንድትተዳደር ለማድረግ ማለትም ሀብቷ ባንድ ላይ ተጠቃሎ ቤተ ክርስቲያኗ በምታዘጋጀው በጀት መሠረት አብያተ ክርስቲያናት እንዲተዳደሩበት በሚል በአቶ ከበደ አበበ ሰብሳቢነት የተቋቋመው ሰባት ታላላቅ ሰዎች ያሉበት ግብረ ኃይል ዕቅድ እንዳይሳካ ያደረገው በረከታቸው ትድረሰንና መቼም ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋምና በግፍ በሰማዕትነት ያለፉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በሚያስተምሯቸውና በሚረዷቸው ሰዎች ምክንያት የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማት ሆነው ነገር ግን ጠቀም ያለ የሆነ የኪራይ ገንዘብ የሚያስገኙ ለግላቸው የሚውሉ ተቋማት ገቢ ወደ አንድ ቋት እንዲገባና ከዚያ እንዲጠቀሙ ሲነገራቸው ፈቃደኛ ባለመሆናቸው መሆኑን ጽፈዋል፡፡
2ኛ. ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ “አንድ አፍታ ላውጋችሁ” በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 246-47 በደርግ ዘመን ከንጉሡ ዘመን ግብረ ኃይል አባላት መካከል ሁለቱን በማካተት በኮሎኔል አጥናፉ አደራጅነት ቤተ ክርስቲያን ከመንግሥት ድጋፍ ወጥታ ራሷን የምትችልበት መንገድ እንዲፈጠር በዶ/ር ክነፈ ርግብ ዘለቀ ሰብሳቢነት የሚመራ ሰባት አባላት ያሉት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ነበር፡፡ ነገር ግን በእነ ሊቀ ማእምራን አበባው ይግዛው ጠንሳሽነት ያልተሰጣቸውን አጀንዳ ፓትርያርኩ ለመንግሥት ሳያሳውቁ አቡነ ጳውሎስን ጨምሮ ሦስት ጳጳሳትን ሾመዋልና ከፕትርክና ይነሱ ብለው ሰበር የሆነ ሰባሪ አጀንዳና መለያየት ምክንያት ይሄኛውም ግብረ ኃይል ውጤታማ ሳይሆን እንደቀረ ጽፈዋል፡፡
3ኛ. በዚሁ በቅርብ ጊዜ ደግሞ በብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ መሪነት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በነበሩበት ወቅት ቤተ ክርስቲያን ዘመኑን በዋጀ የአሠራር መንገድ እንድትጓዝና ራሷን እንድትችል ታቅዶ ጥልቅ የጥናት ሰነዶች ተዘጋጅተው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራት ፭ቱ ከለባት ማኅበረ ቅዱሳን ቦታህን ሊቀማህ መጣብህ በሚል ውክቢያ እንዲዳፈን የተደረገው እንዲሁም የመከነውና በሞዐ ተዋሕዶ ሊዋጥ ሊሰለቀጥ በመንገድ ላይ ያለው ጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት ለምን የተመሠረቱት አላማ ሊያሳኩ አቃታቸው? ብሎ ገምግሞ ያለውን ፈትሾ አጥርቶ የተነሳ ባለመሆኑ ነው፡፡(በፎቶ የቀረበውን የሁለቱን መመሳሰልና አንዱ ሌላውን ይውጠው ዘንድ እንዲገባ ለቡ!)

በርግጥ ኢ-መዋቅራዊ አደረጃጀት እሳት ለማጥፋት፣ የሕዝብን ሥልጣን ይዞ ሕዝብ ላይ የሚያላግጥን ባለሥልጣን ለማስደንገጥና አደብ ለማስያዝ ጠቃሚ ቢሆንም ይህ ዓይነቱ አካሄድ አስተዳደሯ ክህነታዊ ለሆነው ለታላቋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካለመመጠኑም በላይ በማኅበሩ ውስጥ የተሰገሰጉ በጣት የሚቆጠሩ ለቅዱስ ሲኖዶስና ብፁዓን አባቶች ክብር የሌላቸውና ንቀትን የተለማመዱ አካላት አነሳሽነትና ገፋፊነት እየተደረገ ያለ አካሄድ በመሆኑ አደጋው ከባድ ነው፡፡ አንዱ ማሳያ ገና ሲጀምር የፌስ ቡክ ገጹን ከቨር ፎቶ እንኳ የብፁዓን አባቶች ማድረግ ሲገባው የአንድ ሊቀ ጳጳስ ማድረጉ ትዝብት ውስጥ የሚከትና ለጥርጣሬ የሚጋብዝ ነው፡፡
ስለዚህ “ሞዐ ተዋሕዶ ግብረ ኃይል” ከድጡ ወደ ማጡ የሚከተን እንዳይሆን ከሆቴል ወጥቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን፤ ለቤተ ክርስቲያን የማውቅላት እኔ ብቻ ነኝ ከሚለው ግንጥል አካሄድ ወጥቶ ሁሉን አቀፍ እና በቤተ ክርሰቲያን መዋቅር ሥር ሆኖ ተጠያቂነትና ኃላፊነት በሚሰማው መንገድ ለመጓዝ ራሱን ቢያርም መልካም ነው እላለሁ፡፡
ይቆየን!
የካቲት 2014 ዓ.ም