በአቋም መግለጫ ጋጋታ ሀገርንም ሆነ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መታደግ አይቻልም!!!

ተወዳጆች እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የእረፍቷ መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን!!!

በአቋም መግለጫ አወጣጥ ቅደም ትከተል ካልሆነ በስተቀር በቃል የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቆርቋሪ መሳዮች በተግባር ግን ጥቅማቸው እስካልተነካ ጆሮ ዳባ ብለው ከኖሩ፥ አብዛኞቹ ለሠሩትና ወደፊት ለሚሠሩት የኦርቶዶክሳውያን ወጣቶችን ወኔና ሥነ ልቡና የመስለብና የማምከን ሥራ ቤትና ዳጎስ ያለ ገንዘብ ከከተማ አስተዳደሩ በሽልማት መልክ የተቸራቸው፥ ሌሎቹ ድግሞ በማኅበራት ስም ተሰባስበው የቀድሞውን ሥርዓት ነቃፊ መስለው በስውር ግን አሽከርና ተላላኪ ሁነው በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ ደባ ሲፍጽሙ የኖሩ ለአቋም መግለጫ ሲራወጡ ስመለከት ግራ በተጋባ ስሜት ውስጥ ሆኜ ይህችን መጣጥፍ ጣፍኩኝ።

ከፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ጋር የማልስማማባቸው አንዳንድ ነገሮች ቢኖሩኝም ለዛሬ “አንዳፍታ ላውጋችሁ” ከሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 368-9 ላይ የሰፈረ ሀሳባቸውን ተዋስኩኝ።  ምንም እንኳን የእምነቱ ተከታይ ባይሆኑም የፕሮቴስታንት ሚሲዮናውያን በሀገርና በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚፍጽሙትን ደባ “አድናቃፊና ደንቃራዎች” በሚል ንዑስ ርእስ ሥር እንዲህ ሲሉ ገልጠዋል፦

“ወንጌላውያን ነን የሚሉ ሚሽኔሪዎች—የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን፥ በጠቅላላው የኦርቶዶክስን ሃይማኖት የሚጠሉ ወገኖች ኢትዮጵያ የመጡት ችግረኞችን ለመርዳት ወይም ያላመነውን ለማሳመን፥ ወይም የስዊዲን ሚሽኔሪዎች እንደሚሉት  የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ለመርዳት ሳይሆን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን አፍርሶ አዲስ ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት መሆኑን ከነሱው ውስጥ አንዱ በሕልሙ ያየላትን አፍርሶ አዲስ ቤተ ክርስቲያን መሥራት በግላጭ ተናግሯል። ዝርዝሩን እኔና ሌሎች “The Missionary Factor in Ethiopia” በሚል ርዕስ ባሳተምነው መጽሐፍ ውስጥ ማየት ይቻላል። “

እነሱ በግላጭ እንዲህ እያሉ የኛዎቹ ግርግርን እየጠበቁ ውርውር የሚሉ ጥቅመኞችና ቲፎዞ አሰባሳቢዎች ራሳቸው አቋም አልባ ሆነው የሚወጡትም “የአቋም መግልጫ/ማሳወቂያ” ከቤተ ክህነት ቅርጫት ላያልፍ እንዲህ ማዳነቅ መቀባበል ምን የሚሉት ነው??? ምናልባት ይሄ አቋም አልባ መግልጫቸው የዘመናዊ ሙዳየ ምጽዋት ለቃቃሚዎች(youtubers) ፍጆታ ማሟያና ማስተዋወቂያ፥ ሰብስክራይብ ፥ ሼር አድርጉ እያሉ ቁም ስቅላችንን ለሚያበሉን አስተዋጾ እንዲያብረክት ካልሆነ በስተቀር ሀገርንም ሆነ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን  አስቦና አቅዶ ሊያጠፋ የተነሳ አካልን በብጣሽ ወረቀት ጋጋታ ማሸነፍ አይቻልም።

እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው ዛሬ ላይ በመናፍቃን እየተፈጸመ ያለው ግፍ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ የመጣ አይደለም። ኦነግም በለው ሸኔ የግብር አባታቸውን ጸር ክርስቶሰ አቋም ያለውን ሉተርን መስለውና አህለው እንዲብቅሉ ትልቁን ሚና እየተጫወተች ያለችው ብዙም ያልተወራላትና አድፍጣ የጥፋት ሠራዊቶችን ያሰማራችብን የሉተር እናት ጀርመን ናት። እስቲ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ እንፈልግ!!!

  1. ለምን አውሮጳዊቷ ሀገር ወለጋ ላይ ከዛሬ 100 ዓመት በፊት ሆስፒታል ገነባች?
  2. ኦነጎችና ጀርመኖች ምን አዛመዳቸው?
  3. ዛሬ በየደረጃው ያሉ ኢትዮጵያን የሚያስተዳድሯት አብዛኛው መሪዎች በኢትዮጵያ የሉተራን ቤተ ክርስቲያን ክንፍ የሆንችው መካነ ኢየሱስ አባላት የሆኑት በአጋጣሚ ይሆን?
  4. ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትገነጠል የሚሽኔሪዎች ድርሻ ምን ነበር?
  5. የአናሲሞስ ነሲቡን በግእዝ ፊደላት የተጻፈውን የመጀመሪያውን መጽሐፍ ቅዱስ ማን በላቲን ብቻ ወደ ሚል መርሕ ወሰደው?
  6. ??? እያላቸሁ ቀጥሉበት

ደጃዝማች ወልደ ሰማዕት ገብረ ወልድ “ሕይወቴ” በሚል ድንቅ መጽሐፋቸው ገጽ 474-5 በ1966 ዓ/ም የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ይገልጹታል፥-

“ የጊምቢ አውራጃ ቀደም ብለው ሚሲዮኖቸ የገቡበት ስለሆነ ከቀሩት አውራጃዎች ሁሉ ይብልጥ የሚሲዮን ትምህርት ቤቶችና የጤና አገልግሎት ያገኛል።———–በአይራ ጉሊሶ ወረዳ በአይራ መንደር በጀርመናውያን ሚሲዮናውያን የሚካሄደው ሆስፒታል ይገኛል። ጀርመናውያኑ የጤና አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ በእናት አገሩ ላይ እንዲያምጽ፣ ኢትዮጵያዊነቱን በሚያስክድ ፖለቲካ ይመርዙታል። ኦነግ ተጠንስሶ ወደ ቀሪዎቹ የአውራጃው ክፍሎች እንዲዛመት በማድረግ ላይ እንዳተኮሩ ደረስኩብት።—-“ ይላሉ።

ጉሊሶ ማለት የዛሬዋ የሰማዕታት መንደር ናት! ለቡ!!!

ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ በ”መድሎተ ጽድቅ ቁጥር ፫” ገጽ 275-6 ይህንኑ እንዲህ በማለት ገልጦታል፦

“ወደ እኛ ሀገር የመጡ የጀርመን ፕሮቴስታንት ሚሲዮናውያን በዋናነት የሰበኩትም ስለ “ኢየሱስ” ሳይሆን ኦርቶዶክስ ጠል እና ሴማዊ ሕዝብ ጠል የሆነ አስተሳሰብን ማሥረጽ ነበር። ከ100 ዓመታት ኦርቶዶክሳዊነትን  እና ኦርቶዶክሳዊ ማኅበረሰብን የማስጠላት ዘመቻ በኃላም ውጤቱን አሁን በሀገራችን እየተመለከትን ነው።—-ሉተራውያን  የጀርመን ፕሮቴስታንቶች በኢትዮጵያ ላይ ያስቡትን የረጂም ዘመን ዕቅድ ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ይዘመቱበት ሃኖቨር የተባለውን ቦታ የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ በዓይኑ ለማየት ችሏል። እንደዚሁም እነዚያው የጀርመን ሚሲዮናውያን ከእኛው ቤተ ክርስቲያን ካህናትና አገልጋዮች መካከል በስውር እየመለመሉ   ኦርቶዶክሳዊነትንና ኢትዮጵያዊ ማንነትን የሚጸየፍና እንደ ጭቋኝ እንዲመለከት እያደረጉ የሚቀርጹብትን የፕሮቴስታንት ስብከት የጀመሩበትን ቦታም እንዲሁ በምዕራብ ወለጋ ላይ  በዓይኑ  አይቷል።“

እንግዲህ ኦነግ በዳቦ ስሙ በሸኔ የሚፈጽመው እጅግ ዘግናኝ ጭፍጨፋ በማን ትምህርት እና ሥልጠና እንደሆነና ጀርመኖቹ ከአንድ ምዕተ ዓምት በላይ የመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያንን እንዴት እንደተጠቀሙባት ሳሰብ ለእነዚህ ሰዎች የአቋም መግልጫ ምናቸው ነው??? ምንተ ንግበር??? እላለሁ።

አሁን በሥልጣን ላይ በየደረጃው ያሉት ዋንኞቹ መሪዎች ለማስመሰልና ለማደናገር ያህል ዛሬ ላይ የሆነ የጴንጤ ድርጅት ላይ አምልኮአቸውን ይፈጽሙ እኝጂ ዓላማ አንግበው የተነሱት የሉተራን ክንፍ ከሆነችው ከመካነ ኢየሱስ ነው። ያ ማለት የመሥራቾቻው ዓላማና ግብ የሆነው ሕዝቡ በእናት አገሩ ላይ እንዲያምጽና ኢትዮጵያዊነቱን በሚያስክድ ፖለቲካ እንዲመራና እንዲመራ መፈጸም ትይዩ ዓላማቸው ነው ማለት ነው።

ለሁላችንም የሚበጀን ግን ይህንን የክፋት አሠራር አስወግደን ለሁላችንም ማዕከላችን የሰላምና ፍቅር ባለቤት የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አርአያ ተከትለንና ተመልክተን መከባበር፣ መደማመጥና መከባበር እንጂ ሃይማኖተኛ መስሎ ሊያጠፉን የተነሱት የምዕራባውያንን እኩይ ተልዕኮ ተሸክሞ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ለመምራት መሞከር ሩቅ የማያደርስ ጎዳና ከመሆኑ ባሻገር ኦርቶዶክሳዊነትና ኢትዮጵያዊ ማንነትን እየተሠራ ያለውን ግፍ ታሪክና የታሪክ ጸሐፍት በአግባቡ እየመዘገቡት በመሆኑ በደም የጨቀየ የግፍ ታሪክ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ባንትጋ መልካም ነው።

ሌላው ጉዳይ ታላላቅ የኦሮሞ፣ የአማራ፥ የደቡብ እና ከሌሎችም ብሄር የተውጣጡ አርበኞች የገነቧትን ኢትዮጵያ በጽንፈኞች አንድነታችን፣ የህዝብ አብሮነት እንዲፈርስ መንቀሳቀስና ደጉን የኦሮሞ ሕዝብ ከለላ አድርጎ በከፋፍለህ ግዛው መርሕ አማራንና ትግራዋይን እንደ ሕዝብ ደም እንዲቃቡ እንደተደረገ ሁሉ፤ የጀርመኖቹ ምልምል በሆኑ ባለሥልጣናትና የኦነግ( ሸኔ) ሠራዊት የኦሮሞና የአማራ ሕዝብን እንደ ሕዝብ ደም ለማቃባት የሚደረገው ደባና ሩጫ እንዲቆም በጸሎት እየተጉ ቆም ብሎ ማሰብ፣ ማቀድ እንጂ የአቋም መግለጫ ጋጋታ ምን ያህል እንደ አሜባ እንደተበጣጠስን እንጂ ቆራጥንታችንና የዓላማ ሰዎች መሆናችንን የማያሳይ በመሆኑ በአስተውሎት ብንጓዝ እላላሁ።

ይቀጥላል+++

ተጻፈ ጥር 2014

Leave a comment