ጳጉሜን ለሁሉም፣ የሁሉም፣በሁሉም

ሰላም!ሰላም!ወዳጆች

ዛሬ ላካፍላችሁ የወደድኩት ርእሰ ጉዳይ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሀገር አቀፍ የአምስት ቀናት ጸሎት፣ ጾምና ምህላ ማወጁን ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ

  • ምን አገባውና ለምን ያውጃል?
  • ስለ ምህላውና ጾሙ አፈጻጸምና ጥቅም ከማውራት ይልቅ ፓትርያርኩ ለምን መግለጫው ላይ አልተገኙም?
  • ጳጉሜን 1፣2…የእንትን ቀን የእንትን ቀን እያልን ከማክበር በጾም በጸሎት ማሳለፍ ይሻላል ከሚሉ አስተሳሰቦችና አስተያየቶችን ጀምሮ  የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የወሰነው ውሳኔ ጊዜውን የዋጀ መልካም ተግባር ነው እስከሚሉት ዋልታ ረገጥ ሀሳቦች ሲንሰራሸሩ በማየቴ ጥቂት ለማለት ነው፡፡

በእኔ እምነት የሃይማኖት ተቋማትም ይሁኑ ሀገር ከገቡበት ቅርቃር መውጫ ብቸኛ መንገድ የቤተክርስቲያን ጸሎትና ጥበብ በመታመን ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ የመዳኛና ከችግር የመውጫ ተስፋና መንገዷ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ኢትዮጵያ ታበጽእ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር ›› መዝ 67፡31 ፤‹‹ይገንዩ ቅድሜሁ ኢትዮጵያ ወጸላእቱሂ ሐመደ ይቀምሑ፤በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ፣ ጠላቶቹም አፈር ይልሳሉ›› መዝ 71፡9  እንዲል ጠላት ከወረወረው ጦር ከክፉዎች ሴራና ከአባር፣ቸነፈር፣ከወረርሽኝ…መዳን የምንችለው በአግዚአብሔር ታምነን በምናደርገው ጸሎት ነው፡፡ በኮቪድ 19 ምክንያት ከ28 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ያልቃሉ ተብሎ ቢሟረትብንም ኢትዮጵያውያን ወደ ተስፋችን ወደ እግዚአብሔር ተግተን በመማጸናችን ሕዝበ ነነዌን ያሰበ አስቦ አድኖናል፡፡

ምንም እንኳን ቢዘገይም ዛሬም በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አነሳሽነት ለሀገር ሰላምና አንድነት ጾም፣ ጸሎትና ምህላ  መታወጁ መልካም ነው፡፡ ለዚህም የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን በመወከል በብዙ ድካም የሚወጡ የሚወርዱ የጉባኤው ዋና ጸሐፊ ሊ/ትጉሃን ቀሲስ ተጋይ ታደለ የመሳሰሉ ትጉኃን ምስጋና ይገባዋቸል፡፡

የዘንድሮውን የጳጉሜን የጾም፣ ጸሎትና ምህላ መርሐግብር አስመልክቶ ቢስተካከሉ የምንሻቸውን ሀሳቦች  ላጋራችሁ ፡፡

እንዲህ ዓይነት መርሐግብሮች ሲዘጋጁ ብዙ ጊዜ ለኢትዮጵያውያን በሙሉ እንደተዘጋጁ ቢነገርም እውነታው ግን መርሐ ግብሮቹ በደበዘዘ መልኩም ቢሆን ተፈጻሚ የሚሆኑት በከተሞችና ቴሌቪዥን ባላቸው ሰዎች ቤት በከፊል ነው፡፡ ስለዚህ ተፈጻሚ ሆነው ውጤት ማስገኘት እንዲችሉ መርሐ ግብሮቹ ለሁሉም፣ የሁሉም፣በሁሉም መሆን አለባቸው፡፡

  • ለሁሉም፡- ይህ ማለት አብዛኛው የሀገሪቱ ሕዝብ ማለት 80 በመቶው በገጠር ከመኖሩ አንጻር ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን ታስቦ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በጦርነት ወቅት የመጀመሪያው ተጠቂና አገር ጠባቂ ይሄው ከግምት ውስጥ የማናስገባው 80 በመቶው በገጠር የሚኖረው ማኅበረሰብ በመሆኑ ወደ አዋጅ ከመገባቱ በፊት ዛሬም ነገም ቢሆን የምናዘጋጃቸው መርሐ ግብሮቻችን ሁሉ እነዚህን ወገኖች ታሳቢ ማድረጉን በቅድሚያ ማረጋገጥ ይገባል ማለት ነው፡፡
    • የሁሉም፡- ብዙ ጊዜ በቤተክርስቲያናችንም ይሁን በሀገራችን የሚታዩ ችግሮች ምንጭ እኔ ላስብልህ፣ላውራልህ፣ልስራልህ፣ልኑርልህ፣ላስተዳድርህ እና የመሳሰሉ ጽንፍ የወጡ የራስ ወዳድነት መገለጫ ጠባያት ናቸው፡፡ ስለዚህ የምናከናውናቸው የትኛውም ሀገራዊ ጉዳዮችና መርሐ ግብሮች ኅብረተሰቡ የእኔ ብሎ ተቀብሎ ያለነቀፋ በደስታ እንዲተገብራቸውና የሁሉ እንዲሆኑ ቀደሞ አቅዶ መሥራት ይገባል እንጂ ዋዜማ ላይ ደርሶ እኔ ባወጣሁሉህ መርሐ ግብር ተመራ ማለት ወደ ውጤት ከማደረስ ይልቅ የእነሱ እንጂ የእኛ ብሎ ተቀብሎ እንዳይተገብረው ያደርጋልና ለቡ፡፡
    • በሁሉም፡- ካልተሳሳትኩኝ የአሁኑም መርሐ ግብርም ሊከናወን የታሰበው ቴሌቪዥን ላላቸውና የከተማ ሰዎች ሥራ ጨርሰው ሲመለሱ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ነው፡፡ ይሄም እቅዱ ወጤታማ እንዳይሆን ያደርገዋል፡፡ ቴሌቪዥን ያለው ምን ያህሉ የኅብረተሰብ ክፍል ነው? 3ት ሰዓት ላይ ምን ያህሉ የኅብረተሰብ ክፍል ይመቸዋል? ለሚሉ መሰል በርካታ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ የጾም፣ ጸሎትና ምህላ መርሐግብሮቻችን በሁሉም የሀገሪቱ ጫፎች ተደራሽ ሆነው መልስ ማምጣት የሚችሉ መሆን እንዲችሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ትሁን የሀገሪቱ የተለያዩ ተቋማት በሬድዮና በቀላሉ ተደራሽ የሆኑ የመገናኛ ብዙኃን እንደየቦታውና ሁኔታው አመቺ የሆነ ሰዓት በመጠቀም ይህ ታላቅ ሕዝብ በጋራ ወደ ጌታ፣ አምላኩና የፍጥረት ሁሉ ፈጣሪ ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር እንዲጸልይ ሁኔታዎች ማመቻቸት ቀዳሚ ተግባር ቢሆን መልካም ነው፡፡

በአጠቃላይ ይህ ሕዝብ በት. አሞጽ 9፡7 ላይ ‹‹ የእስራኤል ልጆች ሆይ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን? ›› ቅዱስ ዳዊት በመዝ 86፡4 ‹‹… የኢትዮጵያም ሕዝብ እነዚያ በዚያ ተወለዱ›› ተብሎ የተመሰከረለት ታላቅ ሕዝብ በመሆኑ የምናዘጋጃቸው መርሐ ግብሮች ከ20 በመቶ የማይበልጠውን የከተማውን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ከ80 በመቶ በላይ የሆነውን የገጠሪቱ ሕዝባችንን ብዙኃኑን ያማከለ እንዲሆን በትኩረት መሥራት ይፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያዊነቱ ከማይደራደረው የአፋር፣የሶማሌና የጋምቤላ ሕዝብ ጀምሮ የቤተክርስቲያናችንም ይሁን የሀገራችን ገጽታና ጸጋ ለማጠልሸት ከሚሠሩ ጥቂት ምግባረ ብልሹ ሰዎች በቀር አብዛኛው የሀገራችን ሕዝብ በእግዚአብሔር የሚያምን ሰለራሱ ሳይሆን ስለጎረቤቱና ስለወገኑ የሚያለቅስ ደግ ሕዝብ በመሆኑ አስፈሪውን ዘመነ ኮቪድ ጠብቆ እያሻገረን ያለው ጌታ አምላክ የሁሉ ፈጣሪ እግዚአብሔር አምላክ ሰላሙን፣ ፍቅሩን፣ አንድነቱን ያድለን ዘንድ፤

ተንሥኡ ለሰላም!

ተንሥኡ ለፍቅር!

ተንሥኡ ለጸሎት!

ነሐሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም

Leave a comment