ውድ አንባብያን እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ፍልሰተ ሥጋሃ ለማርያም፣ ለበዓለ ትንሣኤዋና ለበዓለ እርገቷ በሰላም አደረሳችሁ!!!
ቅድስት ቤተክርስቲያን የ40 ዘመን የዮዲት ጉዲትን ጭፍጨፋ፣ከ15 ዓመት በላይ የዘለቀ የግራኝ መሐመድ ጭካኔና ዘር የማጥፋት ዘመቻ፣በዚህ በእኛ ዘመን ደግሞ በአክራሪ ወሀቢስቶችና በየመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በተሰገሰጉ ፕሮቴስታንታዊ ጅሀዲስቶች ከሚደርስባት መከራ፣ስደት፣ ግፍና ጭካኔ ባልተናነሰ መልኩ ዛሬ ዛሬ ጥቅምንና ዘውግን መሠረት አድርገው በቤተክርስቲያን መዋቅር ውስጥ በተሰገሰጉ፤ መሠረተ እምነቷን፣ትውፊቷንና ቀኖናዋን ከአንገት አንጂ ከአንጀት በማይበቀሉ ሹመኞች እየደረሰባት ያለው ደባ፤ ተንኮልና የእናት ጡት ነካሽነት ተግባርበየጊዜው እንገታችንን እያስደፋን ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በርግጥ ቤተክርስቲያኒቱ በግለሰቦች ስብዕናና አመለካከት ላይ ያልተመሠረቱ ምዕመናንና ያለ ዕረፍት ስለቤተክርስያኒቱ የሚጸልዩ አባቶች ባለቤት በመሆኗ ዛሬ ድረስ በሕልውና ለመቆየት ችላለች፡፡
አሁን አሁን ግን ይህንን ሕልውናዋን የሚፈታተኑ ስሟን ተሸክመው ቤተክርስያንን በችግሯ እንኳ ስባሪ ፍራንካ የማይሉ፣ ምዕመኑን ግንባሩንና ደሩቱን ለሃይማኖቱ እንዲሰጥ ሲሰብኩ የሚውሉ፤ እነሱ ግን በችግር ጊዜ እንደ ዓይጥ በየስርቻው የሚወሸቁ፤ የግል ጥቅማቸውን ብቻ የሚሳድዱና ልክ እንደ መናፍቃኑ ድርጅቶች በቤተክርስቲያኒቱ ስም የግል አካውንት ከፍተው የሚንቀሳቀሱ ነገር ግን ስባሪ ሳንቲም ፈሰስ የማያደርጉ፤ የሚጎድልባቸው ጥቅም ብቻ የሚያስጨንቃቸው፤ በመዋቅሯ የማይፈተሹ፣ የማይመረመሩና ለሕጓም የማይታዘዙ፤ይባስ ብለው ደግሞ በቤተክርስቲያንና በምዕመኖቿ ላይ የሚደርሱ ሰቆቃዎችንና የጭቃኔ ተግባራት በምስል ወድምጽ በመቅረጽየተቸገሩ ምዕመናንና ገዳማትን እንረዳለን በሚል ሰበብበአካፋ ሰብስበው በሻይ ማንኪያ የሚያቃምሱ እንደ አሸን የፈሉ በርካታ አማሳኞችን ያቀፉ ማኅበራትና ቡድኖች መበራከታቸው ብዙዎቻችንን እያስጨነቀ ያለ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
በእኔ እምነት ለዚህ ሁሉ ነገሮች ከዳረጉን አንዱ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የምትከተለው መዋቅራዊ አደረጃጀት ነው፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲያን ሊኖራት የሚገባው መዋቅራዊ አደረጃጀት ሐዋርያዊ መሆን ሲገባው ሰባኪ መር፣አለቃ መር(ፓስተራዊ) መዋቅር መሆኑ በቤተክርስቲያኒቱከፍተኛ ችግር እያስከተለ መሆኑን በጉዳዩ ላይ የጠለቀ ዕውቀት ያላቸው ሙህራን ይገልጻሉ፡፡ በሐዋ 4፡32 ላይ ‹‹ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ፤አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸው፤ገንዘባቸውምሁሉ በአንድነት ነበረ…›› እንዲል ቅድስት ቤተክርስቲያንን አንዲት፣ ሐዋርያዊት ሊያስብላት ከሚችሉ ነገሮች መካከል አንዱየገንዘብ አስተዳደሯ በአንድ ቋትና የሰው ኃይል አሰተዳደሯም የተማከለመሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የሆነ አስተዳደራዊ መዋቅር ግን ሉተራዊ መዋቅር ነው፡፡ አንድ የእምነት ተቋም በሉተር ግላዊ አመለካከትና አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ከሆነ የራሱን የግል ተቋም ከመሠረተ በኋላ የሰውም ይሁን የገንዘብ አስተዳደሩ በራሱ በሰባኪው(በፓስተሩ) እምነትና ፍላጎት የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ዛሬም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በዚህ ዓይነት አስተዳደራዊ መዋቅር ውስጥ የተዘፈቀች በመሆኗበውስጧ ያሉ የራሳቸው የግል አካውንት ፣ማኅተም፣ አስተዳደራዊ መዋቅር ያላቸው፤ምዕመኖቿንም በሚመቻቸው መልኩ የሚጠቀሙባቸውና የሚግጧቸው የግል ማኅበራትና የግል አብያተ ክርስቲያናት ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ ምናልባት ለአንዳንዶቻችን በማኅበር እየተደራጁ ስም ማጥፋትና ማሸማቀቅ (Character Assassination) አዲስ ነገር ሊመስለን ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ ድርጊት በንጉሡ ዘመን ነበረ፡፡ ይኸውም 50 በሚሆኑ ሆን ተብለው በተደራጁ ማኅበር ጠጪዎች አማካይነት በየመንደሩ እየዞሩ ስም የማጥፋት ዘመቻ በተለይ ደግሞ በቤተክርስቲያን ውስጥ ያልተመቿቸውና የማይገብሩላቸውን ጣፋጩን መራራ፤ መራራውን ጣፋጭ በሚያደርጉ የፊውዳል ባላባቶች ቤተክርስቲያን እረፍት እንዳታገኝ ይሠራ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች እውነተኞቹን የቤተክርስቲያን አባቶች እነ አቡነ ቴዎፍሎስን ሳይቀር የዛሬዎቹ ፌስቡከሮችና ብሎገሮች እንደሚያደርጉት የዛርና የዓይነ ጥላ መንፈስ ነግሶባቸው በየመንደሩ እየዞሩ ስም ሲያጠፉ የሚኖሩ ነበሩ፡፡ የዛሬዎቹም ስም አጥፊ ቡድንተኞችና ማኅበርተኞች ከእነዚህ ከግብር አባቶቻቸው በማኅጸን በተዋረሳቸው የዛርና የዓይነ ጥላ መንፈስ እንደሚንቀሳቀሱ እሙን ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌ 6፡12‹‹ ሰልፋችሁ ከሰማይ በታች ካሉት ከክፉዎች አጋንንትና ከጨለማ አበጋዞች ጋር ነው እንጂ ከሥጋዊ ከደማዊ ጋር አይደለምና›› እንዲል በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን 320 የሚደርሱ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ኪዳን የተቀበሉ ቅዱሳንን ጸሎትና ምልጃ ይዘን እነዚህ በጨለማ አበጋዞች ፤በዛርና በዓይነጥላ መንፈስ የሚዋጉንና ሁልጊዜ የጭቅጭቅ አጀንዳ በመፈበረክ ቅደስት ቤተክረስቲያንን የሚያውኩ የቤተክርስቲያን ነቀርሳዎች የሆኑ ቡድንተኞችንና ማኅበርተኞችን መዋጋት አለብን፡፡ ውድ ክርስቲያኖች ክርስቶስ ነጻ አውጥቶን ሳለ እስከ መቼ በጨለማ አበጋዞች እየተመራንና እየተበጠበጥን እንኖራለን?
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን ወደ በርካታ የሆኑ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበራት ስብስብ እየተንደረደረች(accelerate) መሆኗን ብናውቅም ብዙዎቻችን ይሄንን ለማረም ከመነሳት ይልቅ የቤተክርስቲያን ቀዳዳ(ክፍተት) ተጠቅመን አዋጭ የሆነ፣ ታክስ የማይከፈልበት የግላችንን ማኅበር ለመመሥረት ያሰፈሰፍን መሆኑን ለመረዳት አሁን እንኳ በዚህ ‹‹የለውጥ አመራሩ›› ሀገሪቱን ከተረከበባት ጊዜያት በኋላ ለቤተክርስቲያንና ለምዕመናኑ ችግር አለሁ ቆሜአለሁ በማለት የተመሠረቱትን በርካታ ‹‹ኅብረቶች›› መለስ ብሎ ማየቱ በቂ ነው፡፡


ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ በየጊዜው ለቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ ሆነው ከሚነሱ እያንዳንዱ ማኅበራት ጀርባ የማይቀሩ ግለሰቦችና ማኅበራት መኖራቸው ነው፡፡ እስቲ ሩቅ ሳንሄድ ቋሚ የአደጋ ጊዜ መፍትሔ አፈላላጊ ማኅበራትን ትተን ወደ ኋላ መለስ ብለን በሱማሌና በሐረሪ ክልል በቤተክርስቲያን ላይ የደረሰውን አሰቃቂ ግፍ ተከትሎ እስካሁን የተመሠቱ ማኅበራትንና ቡድኖች በህሊናችሁ አስባችሁ በእነ ማን ተመሠረቱ? ከተመሠረቱ በኋላ ለቤተክርስቲያኒቱና ለምዕመናኑ ምን ፋይዳ አመጡ? አንዱን ማኅበር ከማጠናከርና ከማጎልበት ይልቅ ችግር በተፈጠረ ቁጥር አዲስ ማኅበር ለመመሥረት ጥድፊያና ግርግር ለምን አስፈለገን? የሚሉትን ጥያቄዎች ማንሳቱ ለአንቅሆ ያግዘን ይሆናል፡፡
ከላይ ለመጠቆም እንደሞከርኩት የቤተክርስቲያኒቱ በንጉሡ አጼ ኃ/ሥላሴ ዘመን ከሲሶ መንግሥት ባለድርሻነት መነቀልን ተከትሎ ለተፈጠረው መደናገጥ መፍትሔ ይሆን ዘንድ በአቡነ ቴዎፍሎስ አነሳሽነት የተተገበረው ቃለ ዐዋዲ ጊዜያዊ መፍትሔና እፎይታ ቢሰጥም ዘለቄታዊ ችግርን ግን የሚፈታ ሊሆን አልቻለም፡፡ በወቅቱ እነ አቡነ ቴዎፍሎስ ቃለ ዐዋዲው ጸድቆ እንዲተገበር በማድረግ በፍጥነት የወሰዱት የመፍትሔ እርምጃ ቤተክርስቲያኒቱን ከመውደቅ ለማዳን ችለዋል በዚህም እጅግ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ምንም እንኳ አንዳንዶች ቃለ ዐዋዲውን ለቤተክርስቲያኒቱ ችግር ዘላለማዊ መፍትሔ አድርገው ቢያስቡም በወቅቱ ከነበሩ ሰዎችና የታሪክ ድርሳናት መረዳት የሚቻለው ግን ቃለ ዐዋዲው መሠረት ያደረገውና በከፊል የተቀዳው ከፕሬስባይተርያን (presbyterian)ና ከአንግሊካን (Anglican) ቤተ እምነቶች መዋቅር በመሆኑ ፓስተራዊና ተዋረዳዊ አደረጃጀትን የተከተለ እንዲሆን ሆኗል፡፡በዚህ ላይ ደግሞ ንቡረ እድ ኤርምያስ ከበደ ‹‹ኢትዮጵያ የዓለሙ መፋረጃ!›› በሚለው መጽሐፋቸው ከገጽ 423-425 ‹‹…ከጽንሰ ሓሳቡ አንስቶ፣ ደንቡንና ማብራሪያውን በጽሑፍ አርቅቆ እስከመቅረጽ ፤ከዚያም አስፈቅዶ በአዋጅ እስከማውጣትና በሥራ ላይ ያደረሰው እኔን ትሑት አገልጋዩን መሣሪያ አድርጎ መሆኑን…›› በማለት የገለጹትና ሙሉ ለሙሉ ልፋቴን ለአቡነ ቴዎፍሎስ ተሰጠብኝ የሚለውን ቅሬታቸውን ደምሮ ማየቱ ለብዙ ነገር ይጠቅማል፡፡ በአጠቃላይ ቤተክርስቲያን በዚህ ሕግ ምክንያት ሐዋርያዊ መዋቅር ከመከተል ይልቅ ሕዝባዊ ወይም ተዋረዳዊ ሆነች፡፡ በመሆኑም ቤተክርስቲያኒቱ ሁለት ዓይነት የማይሰናሰሉ አደረጃጀቶች እንዲታይባት ሆኗል ከላይ ቅዱስ ሲኖዶሱ ሐዋርያዊ ትውፊት የሚከተል ሲሆን እታች ያለው ሕዝባዊና እንደ ፓስተሮች በግለሰቦች ላይ የተደገፈ አደረጃጀት ነው፡፡ በዚህም ዛሬ ያሉን ማኅበራትም ከአስተዳደር አንጻር ዘመናዊ ፓስተራዊ አካሄድን የሚከተሉ የኦርቶዶክስ ተሐድሶዎች ናቸው ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ ይህን እንድል ያስቻለኝ ገፊ ምክንያት ደግሞ ማኅበራት ከቤተክርስቲያኒቱ ጋር በምንም መልኩ ያልተሳሰረና ያልተሰናሰለ መዋቅራዊ አደረጃጀት ያላቸውና ቤተክርስቲያኒቱም የማትቆጣጠራቸውና የማታዛቸው አባላትን ያቀፉ፤ በገንዘብ አስተዳደርም ቤተክርስቲያኒቱ የማታዝበት፣የማትቆጣጠረውና የማትመረምሩ የራሳቸው የግል የባንክ ሒሳብ ባለቤቶች በመሆናቸው ናቸው፡፡ ከዘህም በተጨማሪ ማኅበራት በአደጋ ጊዜ የሚለቁት ለእርዳታ የሚሆን ገንዘብ ወደ ሂሳባችን አስገቡልን ማስታወቂያ ከቤተክርስቲያኒቱ ጋር የፉክክር መንገድ ላይ ያሉ እንጂ ቤተክርስቲያኒቱን ለመደገፍ የተቋቋሙ አይመስሉም፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ከዚህ በታች ያለው የእርዳታ ማሰባሰቢያ ማስታወቂያ ነው፡፡




ቃለ ዐዋዲው በተመለከተ በርግጥ በርካታ መልካም ነገሮች ቢኖሩትም የቤተክርስቲያን አይጦችን በተመለከተ ግን መያዣ መጨበጫ ላሳጣን ውንብድና ዝርፊያ እንዲመቻቸው ያደረገና በሥሯ አለን የሚሉ ማኅበራትም ከአስተዳደር አንጻር ፓስተራዊ አካሄድን እንዲከተሉና ኦርቶዶክሳዊ ተሐድሶዎች እንዲሆኑ ያደረጋቸው ይሄው ቃለ ዐዋዲው እንደሆነ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል፡፡
ለመሆኑ በቃለ ዐዋዲ የሚታዩ አስተዳደራዊ ክፍተቶች ምን ችግር እያመጡብን ነው?
በአንድ ወቅት በአውሮፓ እንደ አሸን ፈልተው የነበሩ የፕሮቴስታንት አብያተ እምነቶች የከሰሙትና ቤተ አምልኮዎቻቸውም ወደ ጭፈራ ቤትና ሙዚየም የተቀየሩት በሚከተሉት ፓስተራዊ(ሰባኪ መር) መዋቅር ምክንያት መሆኑ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንም የሚታየው አስተዳደራዊ መዋቅር ከላይ ሐዋርያዊ፤ ከታች ደግሞ ፓስተራዊ(ሰባኪ ወይም አለቃ መር) ቢሆንም ያለወደቀችውና በከበቧት ፈርጀ ብዙ ችግሮች እየተንገታገተች የቆየችው ከግለሰቦች ይልቅ በትክክል በእግዚአብሔር የሚያምኑና የሚታመኑ፤ በቅዱሳን ምልጃና ጸሎት የሚደገፉ መልካም፣ሩህሩህና ቸር የሆኑ፤ ሳይኖራቸው ለቤተክርስቲያን ችግር ነፍሳቸውን እንኳ ሳይሳሱ ያለንፍገት የሚቸሩ፤ ከአገልጋዮች ይልቅ በተሻለ መንፈሳዊ ልዕልና ላይ የሚገኙ ምዕመናን ባለቤት በመሆኗ ነው፡፡ይህ መዋቅራዊ ችግራችን በጊዜው ተፈትሾ ተገቢው እርምት ካልተደረገበት፤ ተገቢውን ትኩረት ያልሰጠነውና ሁሉን ተደራሽ ማድረግ ያልቻለው የወንጌል አገልግሎታችን፤ ስለ ምዕመናን ሁለንተናዊ ሕይወት መሻሻል አለማሰባችንና ደንታ ቢስነታችን እየተጓዝንበት ያለንበትን የቁልቁሊት ጉዞ ከማፋጠኑም በላይ ዋና ሥራችንና መደበኛ ጉዳያችን አድርገን ተተብትበን የተያዝንበት በቡድንተኛ ዘራፊዎችና አማሰኞች ጉዳይ መጨቃጨቅ፣ ዩኒፎርም ለብሶ ሰልፍ መውጣት፣ቢሮ ማሸግ፣ በየብሎጉና ማኅበራዊ ሚዲያው መጠዛጠዝ በዚሁ ከቀጠለ ያለምንም ጥርጥር በርካታ ምዕመናንን መጣታችንና እየጣሉን መውጣቸው አይቀርም፡፡
ከዚህ ቀጥሎ ይሄ ፓስተራዊ(ሰባኪ ወይም አለቃ መር) የሆነ መዋቅራዊ አስተዳደራችን ያስከተለውን ችግርና በማኅበራት ካባ በቤተክርስቲያን የሚፈጸመውን ደባ እንመልከት፡-
ማሳያ አንድ(scenario1) -በውጪ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ
የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያ በዲያስጶራው ዓለም መስፋፋቷ እጅግ አስፈላጊና ጌታችን በማቴ 28፡19 ‹‹ሑሩ ወመሀሩ ኵሉ አሕዛበ…›› ብሎ ያዘዘውን ታላቁን የቤተክርስቲያን ተልኮ ለመፈጸም የሚያስችላት ነው፡፡ ለዚህም ታላቅ ተልዕኮ አጅግ ከባድ በሆነ የአኗኗር ሁኔታ ውስጥ አንኳ ሆነው የደከሙና የሚደክሙ ንጹሐንና እውነተኛ ብጹዓን አባቶች፣ካህናት፣የሰ/ት/ቤት ወጣቶችና ምዕመናን ምስጋና ይገባቸዋል፡፡
በአንጻሩ ደግሞ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በውጭው ዓለም ያላት ባለቤትነት ለይስሙላ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለምሳሌ በሰሜን አሜሪካ ከ10 የማያንሱ አህጉረ ስብከቶች ያሉ ሲሆን በእነዚህ አህጉረ ስብከቶች የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በአብዛኛው በቻሪቲ ስም በግለሰብ ማለትም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሆኑ ቅዱሳንና ብጹዓን አባቶች በግል ስማቸው ሳይቀር፣በቦርድ አሊያም በሆነ ጎጥ ስብስብ የተመዘገቡ፤አንዳንዶቹ ደግሞ በማን ስም እንደተመዘገቡ የማይታወቁና ሲብስ ደግሞ ብጹአን አባቶች ለይስሙላ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ይባሉ እንጂ የማያዙባቸውና የማያስተዳድሯቸው ናቸው፡፡ ቀሳውስቱም፣ዲያቆናቱም ሆኑ ምዕመናኑ የአገልግሎቱ ተሳታፊዎች እንጂ ባለቤቶች አይደሉም፡፡ በአንድ ወቅት በዚሁ በአማሪካን ሀገር የቅዱስ ዑራኤልን ታቦት ለመትከል ፈቃድ ሲጠየቅ በዚህ ስም ቀድሞ በአንድ ግለሰብ ስም የተመዘገበ ታቦት ስላለ አይቻልም መባሉን አስታውሳለሁ፡፡ ታዲያ ከዚህ በላይ ኪሳራና ዝቅት ምን አለ?
ከዚህ በላይ ደግሞ ሰሞኑን አንዳንድ መምህራነ ወንጌልና ፌስቡከሮች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን 2ኛ ዓመት የሰላምና የአንድነት ጉባኤ በሚል የዳቦ ስም ጥናታዊ ጽሑፍ ሲያቀርቡ በቴሊቭዥንና ማኅበራዊ ድረ ገጽ ዜና አድርገው ሲያሠራጩ በዚህ የዳቦ ስም ሲደሰኩሩ ስመለከት አእምሮዬ በጥያቄ ይናጥ ገባ፤ እውነት እውነቱን እንነጋገር ከተባለ፤ የሰላምና አንድነት ጉባኤ ምንድነው? በየትኛው ጉዳይ ነው አንድነት ያለን? በአስተዳደራዊ መዋቅሩ ነው? በሀብትና ንብረቱ? በአብያተ ክርስቲያናቱ? ወይስ በአገልጋዮቹ? ምነው ባናሾፍ!!! እኔ የማምነው በዓሉ መከበር ካለበት ‹‹ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ፣ብጹዓን አባቶችና ፖለቲከኞ ወደ ሀገር የተመለሱበት 2ኛ ዓመት›› ተብሎ መሆን እንዳለበት ነው፡፡ከበፊቱ የተለወጠው አዲሱ ነገር እኮ የብጹዓን አባቶች አንድ ላይ ለስብሰባ መቀመጥና ጥቂት አባቶች እነ አቡነ መቃርዮስን የመሳሰሉ ምነው እስካሁን አብረውን ቢኖሩ ብለን የምንቆጭባቸው የወንጌል ገበሬ፣ እውነተኛና ጀግና አባቶች አገር ውስጥ በሚገኙ ሀገረ ስብከቶች መመደባቸው ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ አንድነት አንድነት እያልን ብናቆለጳጵሰው ጥናታዊ ጽሑፍ አይደለም መጽሐፍ ብናሳትምለት እስካሁን ፍፁምና አማናዊ አንድነት ማለትም አስተዳደራዊ፣ መዋቅራዊ፣ በገንዘብና በሰው ኃይል አንድነት ስሌለን ራሳችንን ማታለል አቁመን መራራም ቢሆን ይህንን እውነት ልውጠው ይገባል!!!
ስለዚህ አማናዊ የሰላምና የአንድነት ጉባኤ ማክበር እንድንችል ሁለንተናዊ አንድነትን(በአስተዳደር፣በመዋቅር፣በሰውና በሀብት አስተዳደር) በጥናት ላይ ተመሥርተን ብናረጋግጥና በቻሪቲ ማዕቀፍ በግለሰቦች ስም የተመዘገቡትንና የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የማታዝባቸውን ንብረቴ ብላ ያልተመዘገበቻቸውን አብያተ ክርስቲያናት ከየሀገራቱ መንግሥታት ሕገ መንግሥት ጋር የሚናበቡ ሕገ ደንቦችን አዘጋጅቶ በማቅረብ አብያተክርስቲያኒቱን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስም የማስመዝገብ ሥራ ብንሠራ በወርቅ ቀለም የሚጻፍ፤ ታሪክ የማይዘነጋው ሥራ ከመሆኑ ባሻገር የሰላምና የአንድነት ጉባኤያቱ በዳቦ ስማቸው ሳይሆን አማናዊና ያማሩ ሆነው በሁላችንም ዘንድ እንዲከበሩ እድል እናገኛለን ማለት ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ሳይነሳ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ ጎጥንና ቡድንተኝነትን መሠረት ያደረጉ በውጩው ዓለም ያሉ ‹‹ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን›› የሚለውን ከአንገት እንጂ ከአንጀት የማያምኑ ተከፋፍለው በጎሪጥና በጥንቃቄ እየተያዩ የሚኖሩ አብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ ነው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ የሚታወቁት ክፍፍሎች በሀገር ውስጥ ሲኖዶስ ሥር ያሉ ፣ በውጪው ሲኖዶስ ሥር ያሉ እና ከምን እንደደሆነ ገለልተኝነታቸው ባይታወቅም ‹‹ገለልተኛ›› ነን የሚሉ ሦስት ክፍፍሎች ናቸው፡፡ አራተኛው ግን ማህበራዊ ሚዲያውንና መገናኛ ብዙኃኑን በተቆጣጠሩ አባላቶቹና ደጋፊዎቹ ተሸፋፍኖና የቆየውና ተደበስብሶ የኖረው በማኅበረ ቅዱሳን የዲቪ ፕሮግራም ተጠቃሚ በሆኑ ግለሰቦች የተመሠረቱ ‹‹የማኅበሩ አብያተ ክርስቲያናት›› ናቸው፡፡ የእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት መሥራቾቹ ሀገር ውስጥ እያሉ በስብከታቸውና በሕይወታቸው የብዙዎቻችንን ቀልብ ገዘተው የኖሩ ስለነበሩ ወደ ውጪ ሀገር ሲሄዱ ለቤተክርስቲያን አንድነት ይሠራሉ ብለን ብዙዎቻችን ተስፋ አድርገን ነበር፡፡ ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆነና በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ እንዳለመታደል ሆኖ እነሱም እየተደራጁ አራተኛው ክፍፍል መሥርተው ቁጭ አሉ፡፡ እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት መሥራቾቹን ከፓርኪግ፣ ከሱፐርማርኬትና ከታክሲ ሥራ ከመታደጋቸው በላይ ለዲቪ ተጠቃሚዎች የኑሮ መሠረትና የሀብት ምንጭ፣ ለሌሎች ደግሞ ማለት የማኅበሩ የዲቪ ወረፋ እስኪደርሳቸው ድረስ ወደ ሀገረ አማሪካ ለሚመላለሱ ሰባኪያን ለኑሮ መደገፊያና ማረፊያነትና በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ እነሱን ለምን ይቅርባቸው? ደግ አደረጋችሁ!!
በነገራችን ላይ ከዚህ የጡመራ መድረክ አባላት መካከል እስካሁን ከማኅበሩ ጋር ብሆን የዚህ ዲቪ ተጠቃሚ እሆን ነበር ብለው የሚቆጩ አልጠፉም፡፡ ታዲያ ይሄንን ሁሉ ጉድ ይዘን ስለ አንድነት ማውራት አያሳፍርም?
ማሳያ ሁለት (scenario 2)፡-በሕጋዊ መንገድ የተመዘገቡና በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያ ስም የሚንቀሳቀሱ ማኅበራት ጉዳይ
እነዚህ ማኅበራት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ያለባትን ቀደዳ ለመድፈንና አገልግሎቷን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻገር ታስበው የተቋቋሙ ናቸው፡፡ ጊዜያት እያለፉ ሲመጡ ግማሹቹ በታሰበው ልክ አገልግሎት የማይሰጡ፤ ሎሎቹ ደግሞ ሸክም እየሆኑ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ በቤተክርስቲያን ሀብትና ንብረት ጡንቻቸውን አፈርጥመው ብጹዓን አባቶችን ሳይቀር በቁጥጥራቸው ሥር በማዋል ራሳቸውም ይሁኑ ከእነሱ ተገንጥለው በወጡ አባሎቻቸው የቤተክርስቲያንን አገልጋዮችና ምዕመናን እያስፈራሩና እያሸበሩ የሚኖሩ፤ በሚፈጠሩ ግርግሮች ሁሉ የቤተክርስቲያንን ሀብትና ንብረት ለግል ጥቅማቸው የሚያጋብሱ ሆነዋል፡፡
አነዚህን ጉዳዮች የበለጠ አፍታቶ ለማሳየት በቤተክርስያን ስር ከተቋቋሙ ማኅበራት መካከል ማኅበረ ቅዱሳንን እንደ ማሳያ አሁን ካለበት የአገልግሎት ቁመና አንጻር በወፍ በረር እንቃኘው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ከቤተክርስቲያን የአገልግሎት ፈቃድ ያገኘው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ ሥር ሆኖ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ከቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ጋር በመሆን ለማስተማር ነበር፡፡
አሁን ግን ጡንቻውን በማፈርጠሙና አቅሙን በማጎልበቱ የሌለበትና የማይገባበት የአገልግሎት ዘርፍ የለም፡፡ ከዚያ ባለፈ ለረጅም ጊዜያት የማኅበሩ ሀብትና ንብረት የቤተክርስቲያን ሀብትና ንብረት ነው እያለ ሲሰብከን የቆየ ቢሆንም በኋላ ግን በእነ አባ ሰረቀ የሚደረገው ዘመቻ እየከበደ በመምጣቱና የገባበት ፍጹም የሆነ ንግድ ሥራ አዋጭና አጓጊ ስለነበር የሀብትና ንብረት ማሸሽ ድርጊት ውስጥ ተዘፈቀ፡፡ ለዚህ እንደ አንድ ማሳያ የሚሆነው የአቡነ ጎርጎርዮስ ት/ቤትን ወደ ሽርክና ማኅበር(Privatize) ከዚያም ወደ ንግድ ድርጅት እንዲገባ ያደረገበት መንገድ ነው፡፡ የአቡነ ጎርጎርዮስ ት/ቤት ሲቋቋመ የነበረው ሰበካ አሁን ድረስ ይገርመኛል፡፡ የወላጅ ስስ ብልት ላይ ትኩረት ያደረገ ዲስኩር ‹‹ልጆቻችን ሙስሊምና ጴንጤ ት/ቤት ለማስተማር እየተገደድን ነው፤ በዕውቀት የበለፀገ፤ በሥነ ምግባር የታነፀ፤ በኢትዮጵያዊ ማንነቱና መልካም ባህሉ የሚኮራ ትውልድ ማፍራት…ብቻ ያልተባለውን ጠይቁኝ፡፡ ዛሬስ? አባቴ ደህና ደሞዝ ተከፋይ ወይም ሙሰኛ አሊያም ባለጠጋ ካልሆንክ አቡነ ጎርጎርዮስ ት/ቤት ልጆችህን ለማስተማር ማሰብ ዘበት ነው፡፡ እንዲያውም አንዲት ወዳጄ አሁን በቅርብ ደውላ እባክህ ማኅበሩ ላይ የምታውቃቸው ሰዎች ካሉ እባከህን በብር(እጅ መንሻ መሆኑ ነው) ይመዘግባሉ የሚባል ስለሰማሁኝ ነው ብላኝ እርፍ፡፡ አቤት ውርደት! ብዬ እጅግ በጣም አዘንኩ፡፡ መራራ ፍሬ ይልሃል ይሄ ነው፡፡ በዚህ ሰዓት ት/ቤቱ ሙሉ በሙሉ በማኅበሩና በግለሰቦች ሼር ለተመሠረተው ለኤስድሮስ የኮንስትራክሽን፤ ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ ተላልፏል፡፡ በዚህ መልክ በየማኅበራቱ የቤተክርስቲያን ናቸው ተብለው ሲሰበኩልን የነበሩ ሀብትና ንብረቶች ስንቶቹ ተላልፈው ይሆን?







የአባላቱን ጉዳይ ስንመለከት በዚህ ቡድን ግምገማ መሠረት ማኅበሩ እስካሁን ያፈራቸው አባላትን በሦስት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡ ይኸውም፡-
- ጳውሎሳውያን፡- ቅዱስ ጳውሎስ በ1ቆሮ 11፡28 ‹‹ የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው፡፡›› እንዲል ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት ማኅበሩ ያፈራቸው አባላት ከሁሉ ነገር በፊት ቤተክርስቲያንን አስቀድመው በማኅበሩ በኩል ተገቢውን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ናቸው፡፡ እነዚህ አባላት ከአሳዳጅነት፣ከሥልጣን ጥምና ከሴረኝነትም የጸዱ ብርቅዬ የቤተክርስቲያን ልጆች ናቸው፡፡ እነዚህ አባላት ምንም እንኳን የማኅበሩ ከሃሳብ መሪነት ማፈግፈግና መስሎ አደር ቤተ ክህነታዊ ጠባይና መልክ እየተላበሰ መምጣቱን ቢያውቁም ቤተ ክርስቲያንን ወደ ከፍታ ሊያመጡ የሚችሉ ሃሳቦችን በማመንጨት በማኅበረሰቡ ውስጥ አስርጾ ተገቢ ለውጥ እንዲመጣ በማድረግ ማኅበሩ ከተለመደው ዓይነት መሥሪያ ቤታዊ የአሠራር ሂደት እንዲወጣ የሚጥሩና የሚለፉ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ለጫናዎቹ መፈጠር ዋነኛው ምክንያት ራሱ ማኅበሩ ቢሆንም ማኅበሩ በአሁኑ ጊዜ ከውጭም ከውስጥም ከፍተኛ ጫናዎች እንዳሉበት ይታወቃል፡፡ እነዚህ አባላት ግን እነዚህን ጫናዎች ተቋቁመው፣ ብሎም ረትተው ለማለፍ የሚታገሉ አንዳንዴ ደግሞ የትላንቱን ውጤታማ የማኅበረ ቅዱሳን የአገልግሎት ጊዜያት በማሰላሰል ነገ የተሻለ ጊዜ ይመጣል ብለው የሚተጉና የሚያልሙ ናቸው፡፡
- ሳውላውያን፡- ቅዱስ ጳውሎስ በገላ 1፡3 ‹‹ በአይሁድ ሥርዓት በፊት እንዴት እንደኖርሁ ሰምታችኋልና፤ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ያለ ልክ አሳድድና አጠፋ ነበር፡፡›› እና ቅዱስ ሉቃስ በሐዋ 7፡60 ‹‹ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር፡፡›› ብለው እንደገለጹልን ምናልባት ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆኑት ማኅበሩ አንከን አልባ፣ ጥፋት ቢኖርበት እንኳ ያለ ንስሐ መኖር እንዳለበት የሚያምኑ፣ ማኅበሩን በጥፋቱ የሚወቅሱና የሚገስጹ ሰዎች ቢገጥሟቸው በነፍሳቸው ተወራርደው ወደ ኋላ የማይሉ፤ ቀፎው እንደተነካ ንብ ግር የሚሉ፤ ስለ ማኅበሩ ሲሉ በድንጋይ ከመውገርና ከማስወገር ወደ ኋላ የማይሉ ለዘብተኞችና ጭፍን ደጋፊዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች መ/ር ዘመድኩን እንደሚለው አፈ ጻዲቆችና አውርቶ አደሮች፤ ከቅድስት ቤተክርስቲያን ይልቅ ለማኅበራቸው ሟቾች ከመሆናቸው በላይ ለእነሱ ቤተክርስቲያን ማለት ማኅበረ ቅዱሳን፤ ማኅበረ ቅዱሳን ማለት ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡እነዚህ አካላት ማኅበሩ ብቻ በቤተ ክህነቱና በቤተክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ አውራ ድርሻ ይዞ እንዲቀጥል የሚመኙና የሚሠሩ ናቸው፡፡ሳውላውያን በቤተክርስቲያን ጉዳይ ከአንድ ሊቀ ጳጳስ ይልቅ የማኅበሩ አመራር አባል በቤተክርስቲያን ጉዳይ ወሳኝ መሆኑን የሚያስቡ ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት ግቢ ጉባኤንና የማኅበሩ ጽ/ቤት እንጂ በአካልም ይሁን በተግባር የቅድስት ቤተክርስቲያን መዋቅሮች የማይረዱና ተሳትፈውም የማያውቁ ምስኪኖች ናቸው፡፡ ውስጣቸው ሳውላዊ ቅናት ብቻ ነው ያለው፡፡እነዚህ አባላት ማኅበሩ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የተቀበለውን ግቢ ጉባኤያትን የማብቃት ሚናውን በአግባቡ ባለመወጣቱ ምክንያት የተገኙ ናቸው፡፡እነዚህ አካላት የውስጡ ችግር ሲባባስ መከረኛውን ተሐድሶ እያነሡ የአባላቱን እና የምእመናኑን ቀልብ በማሳት መኖር የሚፈልጉ ናቸው፡፡ እነዚህ አካላትን ማለት ማኅበሩ ሳይኖር ቤተክርስቲያን እንደ ነበረች፣ ነገም ማኅበሩ ባይኖር ቤተክርስቲያን እንደምትኖር ማስተማርና መመለስ ካልተቻለ አካሄዳቸው ለማኅበሩም ይሁን ለቤተክርስቲያን አደገኛ ነው፡፡




- ድዮጥራጥሳውያን፡- እነዚህ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ 3ኛ ዮሐ 1፡9 ‹‹ወደ ቤተክርስቲያን ጻፍሁ፤ ዳሩ ግን ዋናቸው ሊሆን የሚወድ ዲዮጥራጥስ አይቀበለንም፡፡ ስለዚህ እኔ ብመጣ በእኛ ላይ በክፉ ቃል እየለፈለፈ የሚያደርገውን ሥራውን አሳስባለሁ፤ ይህም ሳይበቃው እርሱ ራሱ ወንድሞችን አይቀበልም፤ ሊቀበሉአቸው የሚወዱትን ከልክሎ ከቤተክርስቲያን ያወጣቸዋል፡፡›› ይላል፡፡
ዲዮጥራጥስ ቅዱስ ዮሐንስን በሚያህል ታላቅ ሐዋርያ የተነቀፈው ስለ ሦስትጉዳዮች ነው፡-
- ሐዋርያትን ያለ ጥሪው ሹሙኝ ብሎአቸው አይሆንም ብለውታል፡፡ ሐዋርያትን የበቃውን ያልበቃውን አያውቁ ብሏቸው ነቅፏቸው ሔዷል፡፡(ለሥልጣን ጥም ሲል ነቃፊ ነበር)
- በእነሱ ላይ የሚናገረው ክፉ ልፍለፋ ሳያንሰው ሌሎችን አትቀበሏቸው እያለ ያሳድም ነበር(አድመኛና አሉቧልተኛ ነበር)
- ሐዋርያትን የሚቀበላቸውን ከቤተክርስቲያን ያስወጣ ነበር(አሳዳጅና የድኅነት እንቅፋት ነበር)
ይሄኛው ምድብ ከ5 እስከ 10 በመቶ የማይበልጡት ማኅበሩ ያፈራቸው አባላት ለምሳሌ እልፍኝ አስከልካይ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፣ እስትንፋሰ ዲያብሎስ ዲ/ን ታደሰ ወርቁ፣ የአማሪካው ክንፍ አደራጁ፣ የፖለቲካ ተንታኙና ቄሱ ኤፍሬም እሸቴ፣ ሐራዊውና ዲጄው አሉላ ጥላሁንና መሰሎቻቸውን የሚይዝ ክንፍ ነው፡፡ እነዚህ አካላት እነሱ ቀብተው ያሾሙት ካልሆነ በቀር ሌሎቹን የቤተክርስቲያን አባቶች የማይቀበሉ፣ሥልጣናቸውንና ጥቅማቸው የሚጋፋ ከመሰላቸው ታፔላ በመለጠፍ ንጹሐን የቤተክርስቲያኒቱን አገልጋዮችን በሐሰት የሚወነጅሉ፣የሚያሳድዱና ሌሎችም እንዳይቀበሏቸው በከፍተኛ ትጋት የሚሰሩ የዘመናችን ዲዮጥራጥሳውያን ናቸው፡፡እነዚህ አገልጋዮች ዛሬ ላይ ከምንደኝነት ወደ አደገኛ ማፍያነት ተሸጋግረዋል፡፡ ሌሎቹን ትቼ ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ ሁለት የቅርብ ጊዜ ክስተቶችን ላቅርብ፡-
ክስተት 1
በሰኔ ወር ውስጥ ጮሌው ታዴ አንድ ቀን አንዱን የፈረደበት አባት ለማስፈራራት ይሁን ለማስረዳት በውል ባልረዳውም ብጹዓን አባቶች መኖሪያ አከባቢ ሲንከለከል አንድ የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ ሊቀ ጳጳስ ብቻውን ያገኙትና ‹‹ይሄኔ የእኛ ጉዳይ ቢሆን ያዙኝ ልቀቁኝ ብላችሁ ሀገር አይበቃችሁም ነበር፤ የእነሱ ሲሆን ግን ትንፍሽም አላላችሁም…›› ብለው በነገር ሸንቁጠውት ለመናገርም እድል ሳይሰጡት ወደ ቤታቸው ይገባሉ፡፡ ያ ወቅት ደግሞ ሦሰተኛው ፓትርያርክ ማለት የቅባቴዎቹ የተሾመበት ጊዜ ነው፡፡ እውነታቸውን እኮ ነው ወላ ምንደኞቹ ሐራዎች፣ዲዮጥራጥሳውያኑም ይሁኑ ፌስቡከሮች ስለዚህ ጉዳይ ትንፍሽ አላሉም፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ ወደ አደባባይ ተጋኖ እንዳይወጣ ስለተፈለገ፤ ቅባቴ በሆኑ ጳጳሳት ጠያቂነት ማለት እኛ በሽምግልና እንይዘዋለን ስላሉ ተከድኖ እየበሰለ ነው፡፡ እኛ እኮ ጉደኞች ነን የዶግማ ጥሰትን በሽምግልና??? ይገርማል እኮ እናንተዬ!!! ወደ ፊት በዚህ ጉዳይ ከአዲስ አበባ እስከ ጎጃም የጀመርነውን ጥናት ስንጨርስ በዝርዝር ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡
እናላችሁ ታዴ ሆዴ በሊቀ ጳጳሱ ተገቢና ወቅቱን የጠበቀ ተግሳጽ አያበደ፣ እየተወራጨና እየተንጨረጨረ ደረጃ ሲወርድ ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻን ያገኝና ‹‹ እገሌ ጳጳስ ማን ስለሆነ ነው የሚናገረኝ? እሰራለታለሁ!...ምናምን እያለ ጳጳሱን ያገኛቸው ያክል ጨፈረበት፡፡ ይህን ጉዳይና እነዚህ ወንደሞቻችን የሚሠሩትንና ያሉበትን ሁኔታ ለአፍታ ሳስብ ወደያው ትዝ የሚሉኝ የየኋቸውና የነበብኳቸው የማፍያ ፊልሞችና መጻሕፍት ናቸው፡፡ በርካታ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች እነዚህ አካላት ታላቁ አባት አቡነ ጎርጎርዮስ የሚያስወቅሱ ሙት አስወቃሾች ናቸው በሚለው ይስማማሉ፡፡ ብጹዕነታቸው እነዚህ ሰዎች በሚሰሩት ነውርና በስማቸው መነገዳቸውን ሲያዩ ነፍሳቸው ምን ትል ይሆን ? ለቅጽበት ተነስተው ቢያገኟቸው ምን ይሏቸው ይሆን? ብለው የሚጠይቁ ብዙዎች ናቸው፡፡
እነዚህ አካላት ልክ እንደ ዲዮጥራጥስ ሹመት ተከልክለው ለራሳቸው የማይገባቸውንና ባልዋሉበት ሥልጣንና ሹመት ሲወስዱ እንደነ በጋሻው መጋቤ ሐዲስነቱን ከየት አምጥቶት ነው ብሎ መውቀስ ክልክልም ነውር ነው እንዴ? እሊህ የዘመናችን ዲዮጥራጥሳውያን በጊዜ ሂደት እንዴት ከቅን አገልጋይነት ወደ ማፍያነት እንዳደጉ ትንሽ ጭልጭል እያለላችሁ ነው? ልቀጥል…
ክስተት 2
ይሄኛው ክስተት አሁን በቅርቡ መ/ር ዘመድኩን የሰኔ 23ቱን አመጽ ተከትሎ እነ ዳኒ ድምጻችሁ ጠፋ እያለ ሲወቅጣቸው እኛም ቢያንስ እናፋልገው ብለን አሰሳ ውስጥ በገባንበት ጊዜ ያገኘነው ክስተት ነው፡፡ ክስተቱ አንዲህ ነው፡-
ምንም እንኳ ታዴ የሞት ሞቱን እዚህ እዚያም የረገጠበትን ዲስኩር ቢያቀርም እነሱ ወዳጄ በአደባባይ ለመጻፍ ለመቃወም አቅም አያግኙ እንጂ የጦፈ ሥራ ላይ ናቸው፡፡ታዴና ዳኒ እየተጣደፉ እየተወራጩ ቦሌ መድኃኔዓለም ካቴደራል ይገባሉ፡፡ በተለይ የታዴ ብስጭቱን ማንም ሰው ከፊቱ ላይ ማንበብ ይችላል፡፡ በሁለቱ ሁኔታ ግራ የተጋባ አንድ ወዳጃችን ማንን ሊያስፈራሩ ነው? ወይም ምን ግዳይ አግይተው? ይሆን እያለ በቅርብ ርቀት ይከታተላቸው ጀመር፡፡ ጉዳዩ ወዲህ ነው፡፡ ‹‹ኀበ ሀሎ ገደላ ህየ ይትጋብኡ አንስርት›› እንዲል መጽሐፍ አንዲት የቢዝነስ አጋራቸው ለካ እበላለሁ ብላ ለሌላው ያጠመደችው መጥመድ ራሷን አንቆ ነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ ላይ ገብታባቸዋለች፡፡ ዲዮጥራጥሳውያን በሰጧት የማይጠቅም ሥልጠና እና በመሠረቱት የቀበሮ ጓደኝነት ተሳስታ በቤተክርስቲያን ጉያ ተደብቃ ካህናት፣ ምዕመናንና የሰንበት ተማሪዎች ላይ ግፍ መስራትና ማላገጥ የጀመረችው ወዳጃቸው ማታለሉና ማጭበርበሩ ሰውን እርስ በእርስ ማባላቱ ይብቃ ብለው በተነሱ የቦሌ መድኃኔዓለም ካቴደራል ቁርጠኛና እውነተኛ የሰ/ት/ቤት አባላትና የአጥቢያው ምዕመናን አጣብቂኝ ውስጥ ገብታ ኖሯል፡፡ እናላችሁ በዋናነት በታደሰ ወርቁ የሚመራው የማፍያ ቡድን በሌሎች አድባራት እንደለመደው ከአንዴም ሁለት ጊዜ የደብሩ አለቃ ወደ ሆኑት ሊቀ ሥልጣናት ቆሞስ አባ ጥዑመ ልሳን ጋር በቀጥታ በመግባት ይቺ ወደጃችን(ዘማሪት ማርታ መሆኗ ነው) ላይ ችግር እንዲፈጠር ያደረገውን የደብሩ ዋና ጸሐፊ መጋቤ ሥርዓት ዮሐንስን በአስቸኳይ እንዲያስነሱ ቀጭን ትእዛዝ ሰጥቶ ይወጣል፡፡ ይሄ ምዕመናንና የሰ/ት/ቤት አባላት ዘንድ ይደርሳል፡፡ እሳቸውም በደረሳቸው ተግሳጽና ማስፈራሪያ ተደናግጠው በጎን ሄደው ‹‹ሄሎ ካሽ›› የሚል ቅጽል ስም የወጣላቸውን የአሁኑን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ዋና ጸሐፊው ይነሳልኝ ብለው አልቅሰው ያመለክታሉ፡፡ በጎን ግን ለምዕመናን በሰበካ ጉባኤ ተነጋግረን ማርታ ላይ ማስጠንቀቂያ ልንጽፍ ተስማምተናል ይላሉ፡፡

ለወትሮው ላሜ ቦራዎች የነበሩትና በእነ ታደሰ እኩይ የሆነ የማፍያ ድርጊት የተበሳጩ ምዕመናንና የሰ/ት/ቤት አባላት ጥያቄ ማንሳት ጀመሩ ታደሰ ማነው? የየትኛው የቤተክርስቲያን የሥራ ክፍል ሹመኛ ነው? ከዘማሪት ማርታ ጋር ያለው ግንኙነት ምድነው? አለቃውስ ቢሆኑ በአንድ ራስ ሁለት ምላስ ሆነው እንዴት ይጫወቱብናል? ብለው በጥልቀት ሲያጠኑ የስላይድ ነጋዴው ታዴ ጮሌው ፣ የዳንኤል ቡችላና አሽከር፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ በየትኛው የሥልጣን እርከን ቦታ የሌለው እራሱን የሾመና ለዘማሪት ማርታም ‹‹ቤተኛ›› አንድም ‹‹ቤትተኛ›› እንደሆነ፤ በዚህም ምክንያት የቦሌ መድኃኔዓለምን ያክል የተሳለመው ቤተክርስቲያን እንደሌለ ይረዳሉ፡፡ ምዕመናኑና የሰ/ት/ቤት አባላቱ በሚሠራው የማፍያነት ተግባር የበለጠ ስለተበሳጩ መዝገብ ቤቷ ዘማሪ ማርታ ከደብሩ መነሣት እንዳለባት ቁርጥ ሀሳብ ላይ ይደርሳሉ፡፡ ዘማሪት ማርታ በደብሩ ላይ በምትፈጽመው እኩይ ተግባር(አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ወደ ፊት በዝርዝር ይቀርባል) ተንገሽግሸዋላ!!!
በነገራችን ላይ ይሄ አለቆችንና የአስተዳደር ሠራተኞችን እየገቡ ማስፈራራት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በቤተክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ተቀጥረው ያሉ አካላት ባይደግፋቸውም እንኳ በግልጽ የማይቃወሟቸው ከሆኑ፤ አሊያም በከፊልም ይሁን በሙሉ ተባባሪ ከሆኑ ወይም እነሱን ደጅ ከጠኑና በራቸውን ካንኳኩ የትኛውም ደብር ቢሆን ገብተው አለቃውን በማስፈራራት አገሌን ወይም አገሊትን ብትነካ ይሄንን ጉድህን እንዘረግፈዋለን በማለት የማፊያ ተግባር በመፈጸም ለወዳጆቻቸው ተቻችሎ የመኖር ውለታ ይውሉላቸዋል፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ብጹዓን አባቶች እንዲሁም በእነሱ ዘንድ አይነኬ የሆኑ በተለይ የሸዋና የጎጃም ዘወጌ ያላቸው ሰዎች ጥፋትም ቢኖርባቸው እንኳ ወይም ችግር ሲገጥማቸው እስከሚላላጡ ድረስ ይረባረባሉ፡፡ከዚያ ውጪ ከሆንክ ትቦጫጨቃታለህ፡፡ የአፈ ቀላጤያቸው የሐራ ተዋህዶ አፍ ማላቀቂያና ማላገጫ ትሆናለህ፡፡ በቃ ይሄው ነው እጣ ፈንታህ!!!
ወደ ቀደመ ነገር እንመለስና እናላችሁ እነ ታዴ ጭሱም በደብሩ አለቃው ተቀባይነት አግኝቶ በምዕመኑ የከሸፈው ሴራ አለመሳካቱን ሲያውቁ ሌላ ሴራ ቀየሱ፡፡ ሰሞኑን ልክ እንደ አዲስ ክስተት ድቤ እየተደለቀለት ያለውን የግብረ ሰዶማውያን ጉዳይ በማንሳት አሳዳጊውንና የተንኮል አባቱ ዳንኤልን በመያዝ ለቤተክርስቲያኒቱ ተቆርቋሪ ናቸው ብለው የሚያምኗቸውን ባለጠጎችን በመሰብሰብ ‹‹እኛ የመጣነው ከአእላፋት ድምጽ የካህናትና ምዕመናን ተናሥዖት ኅበረት ነው (አቤት የኅብረት ብዛት የት ያደርሰን ይሆን?) እና እዚህ ቦሌ መድኃኔዓለም አጥቢያ ውስጥ የግብረ ሰዶማውያን ስብስብ አለ፣ ጸሐፊውንም እላይ ካሉ አባቶች ጋር ተነጋግረን እንዲነሳ ያደረግነው ጥርጣሬ ስላለን ነው፤ ይሄንን ጉዳይ የምትቃወሙ አካላት የእነዚህ ሰዎች ደጋፊዎች ናችሁ ማለት ነው…›› እያሉ ሲፎክሩና ሲያስፈራሩ ዋሉ፡፡
እዚህ ላይ የዚህ ሁሉ ችግር መነሻ በጸሐፊውና በዘማሪት ማርታ መካከል የተከሰተው አለመግባባት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ የቦሌ መድኃኔዓለም ሰ/ት/ቤትና ምዕመናን ‹‹ቁማሩን ቀድመው ስለበሉት›› የነብርን ጅራት አይዙ…እንዲሉ ምንም እንኳን እነ ዳኒ ለጊዜው በስብሰባው ላይ የተቃወሟቸውን ታላላቅና የተከበሩ ሰዎች ለጊዜው ለማሸማቀቅ ቢሞክሩም ቦሌዎች ግን የማፍያው ቡድን ያቀረበውን ሀሳብ ሳይቀበሉ አሳፍረው መለሷቸው፡፡ ዛሬ ላይ የቦሌ መድኃኔዓለም ምዕመናን ሄዳችሁ ብታነጋግሩ እዚህ ላይ ቢጻፍ ጸያፍ የሆኑ ብዙ ነገር ይዘረግፉላችኋል፡፡ ከስብሰባውም በኋላ ሁሉም በአንድ ድምጽ ለካ እነሲህ ሰዎቸ እንዲህ ቀላልና ወራዶች ናቸው እንዴ? ይሏችኋል፡፡ ይህ ሁሉ ድፍረት የሚፈጽሙት በማኅበረ ቅዱሳን ካባ ውስጥ ተደብቀው መሆኑን ስታስብ ደግሞ የማይጠቅም ብስጭት መበሳጨትህ አይቀርም፡፡ እኔ ግን የማይገባኝና የሚገርመኝ ነገር፤ ማኅበሩን ራሱ እንደሚጠሉት፤ ለውድቀቱም እንደሚሠሩ እያወቀ አንድ ችግር ሲፈጠር በቴሌቭዥኑ እያቀረበ የሚያደናብረንና ከአንገት በላይ በሆነ ልፍለፋቸው እንዲፎክሩ፣ እንዲሸልሉና እንዲያደናቁረን የሚያደርግበት ምክንያት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ እነዚህ የእናት ጡት ነካሾች በማኅበሩ ካባ ተደብቀው ቤተክርስቲያኒቱን የማሸበርና የማፍያ ሥራ እንዲሠሩ እድል እንደሚሰጣቸው ጠፍቷቸው አይደለም፡፡ በእኔ እምነት ማኅበሩ በእነዚህ ሰዎችና በመሰሎቻቸው ላይ ያለው አገም ጠቀም የሆነ አቋሙን አስተካክሎ ምዕመናን ከውዥንብር መጠበቅ አለበት፡፡
አንዳንዶቻችሁ ምናልባት ማኅበሩን ራሱ እንደሚጠሉት፤ ለውድቀቱም እንደሚሠሩ ስል ከጭፍን ጥላቻ ወይም ከመረጃ እጥረት ሊመስላችሁ ይችላል፡፡ በፍጹም!!! ልክ እንደከዚህ በፊቱ ማኅበረ ቅዱሳን የኅዳጣን(የዳኒና የጀሌዎቹ ብቻ) ሆኖ እንዲቀጥል፣ እነሱን ስላባረረ ብቻ የማኅበሩ አመራር ደካማ እንደሆነ፣ እኛ ያልጋገርነው…ዓይነት ጨዋታ መሆኗ ነው፡፡ ማኅበሩ የእነሱን ነውር ሸፍኖ የቀን ከሌሊት ህልማቸው እንዲሳካ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ሥር ማስገባት ወይም ፈርሶ ማየት መሆኑን ለመረዳት ራሳቸው ማኅበሩንም አስመልክቶ ከሚጽፉት ጽሑፍና ከሚያራምዱት አጀንዳ ተነስቼ ለማስረዳት ልሞክር፡፡
ታደሰ ወርቁ በፋክት መጽሔት ቅፅ 2 ቁ.6 የሐምሌ 2005 ዓ.ም እትም እና ቁጥር 7 ላይ ‹‹በቄሳራውያን መዳፍ ሥር ያለ አስኬማ›› እና ‹‹የተቋማዊ ለውጥ ጅምሮች›› በሚሉ ርዕሶች ሥር የእናት ጡት ነካሽ ኾኖ ‹‹ማኅበሩ ለሁለቱ ሲኖዶሶች ዕርቀ ሰላም ላይ አሉታዊ እይታ እንዳለው፣ የአዲስ አበባ ሰ/ት/ቤቶችን በተሐድሶ ሰበብ የቤተክርስቲያን ነውጥ አውጆ እንደነበረና አሳድሟቸው አንደነበረ፤ የጥምቀት ተመላሾችን ለራሱ ዓላማና ጥቅም ብሎ ማኅበሩ እንዳደራጃቸው…›› በአደባባይ በድፍረት ጽፏል፡፡ ይሄን ያለ አንደበት ዛሬ ደግሞ የማኅበሩን ቴሌቪዥን ለመደገፍ እየሠራን ነው ይልልሃላ!!! ቀጣፊ ማፍያ ሁላ!!!



ሌላው ዳንኤል ከማኅበሩ የወጣበትን ትክክለኛ የመሠረታዊ ቅራኔ ምንጮች ቢያንስ ሰለ በማኅበሩ ሀብትና ንብረት ስለተሰበሰቡት ማይክሮ ፊልሞቹ፣ የልማት ተቋማት ማናጂንግ ዳይሬክተር በነበረበት ጊዜ ያጠፋቸው ጥፋቶችና ከማኅበር ወደ ግል ስለተሸጋገሩ መጻሕፍትና ንብረቶች ተሸፋፍኖ የቀረበበትና እና በወቅቱ የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ የነበረውና በአሁኑ ሰዓት አማሪካ የሚገኘው የማኅበሩ የዲቪ እድለኛ የሆነው ዲ/ን ሙሉጌታ ኃ/ማርያም በዕንቁ መጽሔት 4ኛ ዓመት ቁጥር 46 እትም ላይ ያደረገው ቃለ መጠይቅ ተከትሎ ዲ/ን ዳንኤል በደጀ ሰላም የጡመራ መድረክ በኩል በጽሑፍ ባቀረበው መልስ ‹‹…ማኅበሩ ስለ ቤተክርስቲያን በቂ መረጃ የሌለው፣ ዋና ሥራውን ትቶ አባላቱን እንደሚሰልል፤አባ ሠረቀንም ይሁን በጋሻውን የሚከሰው ማኅበሩን ስለነኩት እንጂ ለቤ/ክን አደጋ ነው ብሎ አለመሆኑን…›› በመግለጽ «ባልበላው ጭሬ ላፍሰው» የሚለው ተረት በተግባር በማኅበሩ ላይ ሊፈጽም የሚወድ መሆኑን አይተንበታል፡፡









ውድ አንባብያን ሙሉውን ጉግል አድርጎ ማንበብ ማኅበሩ በዳንኤል ልብ ውስጥ ያለውን ቦታና ለወደፊት ያቀደለትን ሴራ በደንብ ለመረዳት ያስችላልና አንብቡት፡፡
የሆነው ሆኖ እነዚህ አካላት በንስሐ ቢመለሱ ለቤተክርስቲያኒቱ ሊጠቅሙ የሚችሉ ሊሆኑ ስለሚችሉ፤ እነዚህን ከአገልጋይነት ወደ ማፍያነት የተቀየሩ የዘመናችን ዲዮጥራጥሳውያን መክረን ዘክረን ብንመለስ አይሻልም ጎበዝ? እኔ ግን በበኩሌ እስኪመለሱ ድረስ አልፋታቸውም፡፡
ማኅበሩም ለተመሠረት ዓላማ የሚገዛ ሆኖ እንዲቀጥል የማኅበሩን ካባ ለብሰው ምዕመናንና አገልጋዮችን የሚያሸብሩና የሚያሸማቅቁ አመሳኝና ማፍያ የሆኑ ዲዮጥራጥሳውያን ነቅተንባችኋልና ካባችንን አውልቁ ሊል ይገባል፡፡ ማኅበሩን ባለመረዳት የሚያሰደቡት ሳውላውያንን የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና በመስጠት፤ ማኅበሩ ሳይኖር ቤተክርስቲያን እንደነበረች፣ ነገም ማኅበሩ ባይኖርም ቤተክርስቲያን ለዘላለም እንደምትኖር በማስረዳት ከሳውላዊነት ወደ ጳውሎሳዊነት መመልስ አድካሚ ቢሆንም የግድ በፍጥነት ቅድሚያ ተሰጥቶት መከወን ያለበት ጉዳይ ነው፡፡
በዚያ ላይ ማኅበሩን ዋጥ ስለቅጥ አድረገው ሊበሉ ለተዘጋጁ ሰርጎ ገቦችና ለቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ ነን የሚለውን ታፔላ ለጥፈው እንደአሸን እየፈሉ ያሉ፤ ስምና ቁጥራቸው የበዙ ማኅበራት ጀርባ የዲዮጥርጣሳውያ ስውርና ግልጽ እጅ መኖሩ ስታይ የማንቂያ ደውል አትልልኝም!
ማሳያ ሦስት (scenario3)፡-በሕጋዊ መንገድ ያልተመዘገቡና በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያ ስም የሚንቀሳቀሱ ማኅበራት ጉዳይ
በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ትውፊት መሠረት በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚሰባሰቡ፤ እምነትን በተግባር ለመለማመድ የሚያግዙ፤ በክርስቲያኖች መካከል ማኅበራዊ መስተጋብርን የሚያጠናክሩ እንደ ጽዋ ማኅበራትና ሰንበቴዎች የመሳሰሉ ክርስቲያናዊ ስብስቦች አሉ፡፡ እነዚህ ስብስቦች በአንድም በሌላ መንገድ ለቤተክርስቲያን ድጋፍና አስተዋጽኦ ሲያደርጉ የኖሩ ናቸው፡፡
ከኢትዮጵያ እስራ ምእት በኋላ ፳፻፪ ዓ.ም የጥምቀት በዓልን ተከትሎ ወጣቱ ወደ ቤተክርስቲያን ለመመለስ ያሳየው ፍላጎት፣ ተነሳሽነትና የአገልግሎት ትጋት ትልቅ ተስፋን በውስጣችን ያጫረ ነበር፡፡ ኋላ ግን ወጣቶቹ ቤተክርስቲያን ያላት መዋቅር ማንም ተነስቶ የእገሌ ወእገሊት ማኅበር ብሎ ያለፈቃድ ለማቋቋም እና የግል ጥቅም ማጋበሻ ሊውል የሚችል ወተቷ የማይነጥፍ የፈረጅ ላም መሆኑን በተረዱ አማሳኝ መሪዎች መዳፍ ሥር ስለወደቁ ለቤተክርስቲያን አደጋና ችግር እየሆኑ መጡ፡፡ መጀመሪያ አከባቢ እነዚህ በድንገት እንደ ደራሽ ውሃ የመጡ ወጣቶችን በተለያዩ ሰ/ት/ቤቶች በኩል አስተምሮ ወደ መደበኛ አገልግሎት ለመቀላቀል ከፍተኛ ፍላጎትና ጥረት ቢደረግም እነ ፌቨን ዘሪሁንን በመሳሰሉ ጥቅማችን ይቀርብናል ብለው በሰጉ ሆድ አደር ተለጣፊዎች መክኖ ቀርቷል፡፡ አሁን አሁንማ አንዳንድ አለቆች ከሰንበት ተማሪዎች ጋር ሲጣሉ እንደማስፈራሪያ ይጠቀሙባቸዋል፣ በየአገልገሎቱም ላይ ዩኒፎርም የለበሱ ሰንበት ተማሪዎችንና ማኅበራቸውን የሚገልጡ ባጆችና አንጸባራቂ ሰደሪያዎች ያደረጉ በተቀራራቢ የዕድሜ ክልል ያሉ ወጣቶችን ከነ ጎፌሬያቸውና የሴቶች ታይት ከመሰለ ኢ-ክርስቲያናዊ አለባበሳቸው በአገልግሎት ላይ ጎን ለጎን ተሰልፈው ማየት ብርቅ አይደለም፡፡




እነዚህየጥምቀት ተመላሽ ወጣቶች የሌላቸውን የማኅበርና የአባላት ብዛት እየጠቀሱ ጡሩንባ መንፋታቸውን ረስተን በቤተክርስቲያን አገልግሎት ላይ እያደረሱ ያሉትን ሦስት አደገኛና ፈታኝ ሁኔታዎች እንመልከት፡፡
- የመጀመሪያው ማንም ኦዲት የማያደርገውና የገጠር ቤተክርስቲያን ማሠሪያ፤ ለጥምቀትና ለተለያዩ በዓላት ማክበሪያ በሚል ሰበብ ከሀገር ውስጥ እስከ ውጪ ካሉ ምዕመናን ገንዘብ በገፍ ይሰበስባሉ፡፡ ይሄ ገንዘብ ከሦስት ተሰንጥቆ በዛ የሚለው አንዱ እጅ ለግል ኪስ ይውላል፡፡እዚህ ላይ ፌቨንና ጓደኞቿ የጀመሩትን የኢምፖርት ኤክስፖርት ንግድ ሥራ በርቱልን ብሎ አለማለፍ ምቀኝነት ስለሚሆን ግፉበት ብለናል፡፡ሌላው እጅ በጣም ትንሹ ለበዓል ማክበሪያ ሲውል፣ ሌላኛው ሲሶው ደግሞ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ውስጥ እንደፈለጋቸው መንቀሳቀስ ይችሉ ዘንድ አንዳንድ ጥቅመኛ አለቆችንና አገልጋዮችን መግዣ አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡
- ሁለተኛው እነዚህ ወጣቶች በአብዛኛው የቅድስት ቤተክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖናና ትውፊት በተገቢው መንገድ ያልተማሩ በመሆናቸው በቤተክርስቲያን አገልግሎት ላይ ሲሳተፉ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ለመጠበቅ የማይገደዱ በመሆናቸው ወደ ቤተክርስቲያን ለሚመጡ ታዳጊዎችና ወጣቶች አርአያነታቸው የወረደና ምናልባትም ውጪ ያሉ ወጣቶች ያሉበት የሥርዓተ ቤተክርስቲያን ጥሰት በቤተክርስቲያን የተፈቀደ እስኪመስል ድረስ ለሥርዓተ ቤተክርስቲያን የማይገዛ ፍሬ አልባ መራራ ትውልድ እናፈራበታለን ማለት ነው፡፡
- ሦስተኛው አንዳንድ የሥነ ምግባር ጉድለት የታየባቸውን የሰ/ት/ቤት አባላት በሕጉ መሠረት ለማስተካከል ሲሞከር በማኩረፍ በማንኛው ነገር ቁጥጥርና ክትትል ወደ ሌለበት የማኅበራት ኅብረት ዋሻ ሄዶ መሸሸግ የተለመደ ሆኗል፡፡ አሁን አሁንማ በአንዳንድ አጥቢያዎች ሰንበት ት/ቤትን ያገለለ የስብከተ ወንጌል ጉባኤ እስከ ማዘጋጀት ተደርሷል፡፡ ይሄ ደግሞ ሄዶ ሄዶ ከቃለ ዐዋዲው ውጪ በሆነ መንገድ ሁለት የተለያየ ሥርዓትን የሚያራምዱና የሚከተሉ ሁለት የተለያየ መዋቅር ያላቸው በጎሪጥ የሚተያዩ በተመሳሳይ ዕድሜ ያሉ ወጣቶች በአንድ አጥቢያ እንዲኖሩ አድርጓል፡፡ በዚሁ ምክንያት በተለያዩ አድባራት በሁለቱ የወጣቶች ስብስብ መካከል ግጭቶች የሚስተዋሉ ሲሆን ወደፊት ደግሞ ይሄ ግጭት ተባብሶ ወደ አላስፈላጊ ነገር ሊያመራ እንደሚችል በርካታ ጠቋሚ ነገሮች አሉ፡፡
ሌላው ደስ የማይለው ነገር እነዚህን ወጣቶች በማደራጀትና ሥልጠና በመስጠት የማኅበረ ቅዱሳን ስም በተደጋጋሚ የመነሳቱ ጉዳይ ነው፡፡ እንዲህ ተባለ እንዲያ እነዚህ ወጣቶች በአግባቡ መክረንና አስተምረን ወደ መስመር መስገባት ካልቻልን ነገ ለሚፈጠረው ቀውስ ከታሪክም ይሁን ከኅሊና ተወቃሽነት ሁላችንም ማምለጥ አንችልም፡፡ እነዚህ ወጣቶች የቤተክርስያኒቱ መሠረተ እምነት፣ ትውፊትና ቀኖና ሳይማሩ ወደ አገልግሎት የተሰማሩ በመሆናቸው ሥርዓተ ቤተክርስቲየንን ሳይጠብቁ ከነጎፈሬያቸው፣ ከነ ታይት ሱሪያቸው ቢያገለግሉ፣ በቅዳሴ ሰዓት ሰዎች ሲያስቀድሱ ቁጭ ብለው ብናያቸው አሊያም የግል ወሬን እያወጉ ብንመለከታቸው ብዙም የሚደንቅ አይደለም፡፡
ዛሬ ላይ የማንቂያ ደውል ሆኖ ልብ ልንለው የሚገባው ነገር እነዚህ ወጣቶች ዛሬም ይሁን ነገ ላይ ተነስተን በቃለ ዐዋዲው ምዕ 3 አንቀጽ7፡1መ እና አንቀጽ12፡5 መሠረት ወደ ሰ/ት/ቤት መጠቃለል አለባችሁ ብንላቸው የሚሰሙን ይመስላችኋል? ለየትኛው የቤተክርስቲያን አካል ታዛዥ ይሆኑ ይሆን? እኔጃ እኔ ግን እጅግ እፈራለሁ፡፡ ብቻ ጊዜ ይመልሰው!!!





የዚህ የጡመራ መድረክ አባላት ዓላማ የቅድስት ቤተክርሰቲያን ልጆች ከእኩይ ተግባራችን ተመልሰን ለኢትዮጵያና ለቤተክርስያን ትንሣኤ በጋራ እንድንሠራ የማንቃት ሥራ ለመሥራት እንጂ አንዱን አሞግሶ ሌላውን አንኳሶ ለማቅረብ፤ ማንንም ለማሳጣት ወይም ለማሸማቀቅ ባለመሆኑ እግዚአብሔር አምላክ ለሁላችንም ለቤተክርስቲያን ሕግና ሥርዓት የሚገዛ ቅንና እውነተኛ ልቡናና መንፈስ ያድለን!!! አሜን፡፡
ይቆየን
ሳምኬት ነኝ
ተጻፈ ነሐሴ 21 ቀን 2012 ዓ.ም