እንደምን ከረማችሁልን ውድ አንባብያን! እንኳን ለጾመ ፍልሰታ በሰላም አደረሳችሁ!!!
መቼም የቤተክርስቲያን ጉዳይ ልተወው ብትልም አይተውህም ምክንያቱም ቅድስት ቤተክርስቲያን ሕይወታችን፣ክብራችን፣ውበታችና ጌጣችን በአጠቃላይ ሁሉ ነገራችን ስለሆነች!!! እናላችሁ ወረርሽኙ፣ የሀገሪቱ ሁኔታ፣ ቤተ ክርስቲያን ያለችበት ሁኔታ፣ በምዕመናን ላይ የሚደርሰው ግፍ…በማየት ይሄ ጊዜ ዝም ተብሎ በጸሎት የሚታለፍ ጊዜ ነው ብለን የዚህ መጦመሪያ መድረክ አባላት ለጊዜው ከመጻፍ ታቅበን ነበር፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ጳውሎስ በሐዋ ሥራ 20፡29-30 ላይ ‹‹ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ…›› ብሎ እንደነገረን በዚህ ወረርሽኝ ጊዜ እንኳ ስለ ምዕመናንና ስለ ካህናት የሰቀቀን ኑሮ መጨነቅ ሲገባቸው ሰለቀረባቸው የሙዳየ ምጽዋት ግልበጣና በየዳንኪራውና መሸታ ቤቱ ስለቀረባቸው አስረሽ ምችው ብቻ በማሰብ በሚኖሩትየአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሹማምንትና ለወረርሽኙ ተብሎ የተቋቋመው ተስፋ ልዑክ መካከል የተከሰተው ውዝግብ ትኩረታችንን በመሳቡ ወደ መጻፍ መመለስ እንዳለብን ወሰንን፡፡ ውዝግቡ ወደ ውስጥ ሲፈተሽ በርካታ አስቀያሚና አሰፋሪ ነገሮች ቢኖሩትም የበለጠ ውዝግቡን ያጦዘው ግን በቤተክርስቲያን ችግር ላይ የክፋት፣ የተንኮልና የሴራ አጀንዳ እየፈበረከ ቤተክርስቲያን እረፍት እንዳታገኝ የሲኖዶስ ስብሰባ በመጣ ቁጥር እንደተከፈላቸው መጠንና ለአይነኬ ዘውጌዎች ብቻ ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረጉ አጀንዳ እየፈበረኩ ነገር በሚያራግበው የሐራ ዘተዋሕዶ ጸብ አጫሪ ጽሑፍ መነሻ ነው፡፡
ብዙ የተባለለት ነገም ብዙ የሚባልለት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እያደረሰብን ያለው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ ቀላል ባይሆንም በአንጻሩ ደግሞ ያመጣልን አዎንታዊ ጥቅሞች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ለዛሬ አንዱን ማየት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
እንደሚታወቀው በዚህ ቫይረስ ምክንያት ከሰፈር የጉልት ገብያ ጀምሮ እስከ ዓለም አቀፍ ታላላቅ ኩባንያዎች በወረርሽኙ ያልተነካ የለም፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ተጽእኖ ከደረሰባቸው ተቋማት መካከል አንዷ እናት ቤተክርስቲያን ናት፡፡ ምንም እንኳን እስካሁን የሰማሁት የቀነሰችው የሰው ኃይል ባይኖርም ካህናትና የካህናት ቤተሰቦች ግን እያሰሙት ያለው እሮሮና ነገስ? የሚለው ጥያቄ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡አንዳንድ የምንቀርባቸው ካህናት የንስሐ ልጆቻቸውና ብጹዓን አባቶችን ሳይቀር ደጅ መጥናትና አፍጦ ቸግሮኛል የምታደርጉትን አድርጉ ብሎ ለልመና መውጣት ሌላው የታየ አሳቃቂ ነገር ነው፡፡ በየደጃፎቻቸው የተለጠፉ የየአብያተክርስቲያናቱ ወደ አካውንት ብር አስገቡልን የተማጽኖ ደብዳቤና ከዚህ ባለፈ ደግሞ በሀገር ውስጥም ይሁን በውጪ ያሉ ካህናት ከተረጂ ሰዎች(የደሀ ደሀ ተብለው ከተመደቡ) ጋር ለእርዳታ ተሰልፎ መታየት ሌላው አንገት ያስደፋን ጉዳይ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ በርካታ የኪራይ ሱቆችና ቤቶች ባላቸው አብያተክርስቲያናት ጭምር መሆኑን ማየት እጅግ ያስለቅሳል ያበሳጫልም!!!
ለምን ግን ይሄ ሁሉ ሆነብን? ባለ ራዕይ፣ ተስፈዮችና ተራማጅ የሆነ ሀሳብ ባለቤት የሆኑ ወንድሞችና እህቶች እናት ቤተክርስቲያን እኮ ለሀገር ሊተርፍ የሚችል አቅም አላት፤ የራሷ ባንክና የተለያዩ ትልልቅ ድርጅቶችን መመስረት ትችላለች ብለው አልነገሩኝም እንዴ? ለተጨማሪ አንድ ወር እንኳን የሚሆን የደሞዝ ክፍያ እንዴት አጣን? የወረርሽኚ ጊዜ ቢራዘምስ? እንደ ሌሎቹ ሀገራ ሙሉ ለሙሉ ከቤት መውጣት አይቻልም ቢባልስ? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ስለከበደን የዚህ መጦመሪያ መድረክ አባላት መረጃ ለመሰብሰብ ቢያንስ ትልልቅ ወደ ሆኑ አብያተ ክርስቲያናት ለቅኝት ተሰማራን፡፡ የሁላችንም የተሰበሰበ መረጃ የሚጠቁመው በአብዛኛው አብያተ ክርስቲያናት የሚሰማው ድምጽ አንድ ነው ይኸውም፡-
አምስቱን ከለባት ኮረና ጉድ ሠራቸው! ተዋርደው አዋረዱን! የሚል ነው፡፡ ሆይ ጉድ! (በነገራችን ላይ አምስቱ ከለባት የሚባሉት ሙዳየ ምጽዋት ገልባጮች፣ ነውረኞች፣ራስ ወዳድ፣ መሸተኞች፣ሴሰኞች፣ሆድ አደር..የሆኑ በየደብሩ የሚገኙ አለቃ፣ጸሐፊ፣ሒሳብ ሹም፣ ቁጥጥር እና ገንዘብ ያዥ ናቸው፡፡ በግብራቸው ውሻ ተብለዋል፡፡ራዕ 22፡15)
በአዲስ አበባ ያለውን የሰው ሀብትና የፋይናንስ አስተዳደር ብልሽትና ዝቅጠት ለማስተካከል ከዚህ በፊት ብዙዎች የጮኹለት በሎም ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ሞክረው በዛር መናፍስት አንጋሽነትና በጋኔናዊ ትብትብ አሠራር በተካኑ ሆድ አደር የአዲስ አበባ አለቆች የከሸፈው የቤተክርሰቲያን አባቶችና ልጆች ድካም መና ባይቀር ኖሮ ከዚህ ሁሉ ውርደት በታደገን ነበር፡፡ ለነገሩ ልብ ከሰጠን ይሄም የማንቂያ ደውል ነው!
ለምን አንዲህ ዓይነት ችግሮች ተከሰቱብን? ለሚለው ጥያቄ ጥቂት መልሶችና መፍትሔዎች እንመልከት፡-
- በአንድ ቋት ያለመተዳደር ችግር፡- ለብዙዎቻችን ይሄ ሀሳብ ዛሬ የተወለደ ሊመስለን ይችላል፡፡ በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘመን ተነስቶ ሆድ አደር ጥቅመኛ መንፈሳዊ ሹማምንት ተረባርበው አክሽፈውታል፡፡ንጉሡ ‹‹ሃይማኖት የግል ነው ሀገር የጋራ ነው፡፡›› አዋጅ ለማወጅ የተገፋፉት በዚህና በተያያዥ ጉዳዮች ፖለቲከኛ ካህናት ያሳዩት አቋም ሳይሆን አይቀርም የሚሉ አሉ፡፡ቤተክርስቲያንን የማዳከም ሥራ የጀመረው ማነው?ለሚለው አንዳንዶች አጼ ኃ/ሥላሴን ያደርጋሉ፡፡ ለእኔ ግን ትላንትም ዛሬም ቤተክርስቲያንን ለዚህ ችግር የዳረጓት ቤተክርስቲያንን ኃ.የተ.የግ.ማኅበር አድርገው የሚኖሩና ለዚሁ የሚሠሩ ጥቂትና ሆድ አደር የሆኑ የየአብያክርስቲያናቱ አለቆች እና ጀሌዎቻቸው ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ በእኔ እምነት ተጠያቂዎቹ የአዲስ አበባ ካህናት ጭምር ናቸው…ከጥቂት አመታት በፊት እንኳን የነበረውን የፋይናንስ አስተዳደርን የማስተካከል እንቅስቃሴ ማኅበረ ቅዱሳን ከሥራህ ሊያፈናቅልህ… ነው ሲባሉ እንዴት? በምን አቅም? ማለት ሲገባ ማለቴ ቢወስዱ እንኳ የአምስቱ ከለባትን ቦታ እንጂ የቀዳሹን የአወዳሹን ቦታ አልነበረም፡፡ ከለባቱ ግን መጡብን ሊመጡብን ነው ከማለት ይልቅ መጡብህ ሊመጡብህ ነው ብለው የሁል ጊዜ የችግር ገፈት ቀማሽ ምስኪን ካህናትን በማደናገር እኩይ ተግባራቸውን አጠናክረው ለመቀጠል አወናበዷቸው፡፡ ታሪካዊ ስህተት!!!
ስለዚህ ለቤተክርስቲያን በትክክልና በእውነት የምናስብ ከሆነ በአንድ ቋት የመተዳደር ጉዳይ እንደገና በጥናት ላይ ተመሥርተን አጥብቀንና ጠንክረን መጀመር አለብን! ስለዚህ ሳንሰለች መጮህ አለብን!!!
2.በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ያለው የላሸቀ የሰው ኃይል አስተዳደር፡-በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚሾሙ ሥራ አስኪያጆች ልባቸውና አእምሮአቸው ላይ ተነቅሰው ሥራ የሚጀምሩት ‹‹ሲሾም ያልበላ..›› የሚለውን ነቀርሳ የሆነ ተረትና ምሳሌ ይመስለኛል፡፡ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ታሪክ ከንብረ ዕድ ቆሞስ አባ ገ/ማርያም በስተቀር በቤተክርስቲያን ላይ ያላላገጠና ሀብቷን ያልዘረፈ ሥራ አስኪያጅ አላየሁም፡፡ እንደአለመታደል ሆኖ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከየአድባራቱ በታላቅ ጉጉት የሚጠበቀው ሪፖርት የበጀት፣የሥራ አፈጻጸም አሊያም የልማት ሪፖርት ሳይሆን ስንት ሰው ሞተ? ወይም ስንት ሰው ሥራ ለቀቀ? ነው፡፡ ምክንያቱም በአንድ አጥቢያ በአንድ ሞተ ከዳ በትንሹ እስከ ሦስት ሰው መላክ ይቻላል፡፡ በዚህ ደግሞ ብዙ መላ(ፍራንካ) ይሰበሰብበታል፡፡ በእኛ ቤት አንድ ሰው በደጅ ጠኚነት ቆይቶ ሰው ሲሞትለት ወይም ሲለቅነት ሁለት ጊዜ ቀረጥ ተቀርጦ(የድጋፍ ደብዳቤ ለተጻፉለትት ለ5ቱ ከለባት እና ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሹማምንት) ነው የሚቀጠረው፡፡ ይህ ደግሞ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን በዓለማችን ላይ በሰው መሞት ወይም ስንብት ተስፋ የሚኖር ብቸኛው ተቋም ያደርገዋል ማለት ነው፡፡
ለዘመነ መሳፍንት መነሳት ዓይነተኛ ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው ለጉዳዮች ከማዕከላዊ መንግሥት የተማከለ ምላሽ ማጣት መሆኑን ብዙ የታሪክ ሊቃውንትና ጸሐፍት ይስማማሉ፡፡ ዛሬም ቤተክርስቲያን በሰው ሀብትና በፋይናንስ አስተዳደር የተማከለ አሠራር ስሌላት…የምናያቸው ያፈጠጡ ችግሮች በአፍጢማችን እያዳፉን ስንወድቅ ስንነሳ አለነው፡፡
ስለዚህ በመንፈሳዊ ኮሌጆች የሚማሩ ደቀ መዛሙርትም ይሁኑ ስለ ቤተክርስቲያ ከግላዊ ጥቅምና ከዘውጌነት በጸዳ መልኩ በአንድ አጥቢያ ሊኖረው ስለሚገባ የሰው ኃይል እና የፋይናንስ አስተዳደር ላይ የጥናት ወረቀቶችን በማዘጋጀት ለቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የሚሆን ግብአት በማቅረብ ዘለቄታዊ መፍትሔ በጋራ ካልፈለግን በቀር እየተሸማቀቅንና እያለቀስን እንቀጥላለን ማለት ነው፡፡ለዘመናት የዘለቀው ለብልሹ አሠራር መሠረት የሆነው የሞተ ከዳ ዘመናዊ የቅሸባ ቢዝነስ በዚሁ ከቀጠለ የአስተዳደር ልሽቀቱ፣ የእኛም ልቅሶ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡
3.ተጠያቂነት የጎደለው የሥራ ኃላፊዎች ዝውውር፡-በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚመደቡ አለቆች ሥልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው፡፡ በአብዛኛው አንድ አለቃ(አምስቱ ከለባት) መቼና በምን ምክንያት እንደሚቀየር ሀገረ ስብከቱና አለቆቹ ብቻ በውስጥ መስመር የሚያውቁት በመሆኑ አንድ አለቃ ከግብረ አበሮቹ ጋር የሚፈለገውን ያክል ከዘረፈ በኋላ ያለ ተጠያቂነት እንዳካበተው የዘረፋ ሥራ ልምድ ሁኔታ ወደ ሚቀጥለው ከፍ ያለ አሊያም አነስ ያለ ደብር እንደሚዘዋወር ሰለሚያውቅ እንደ ልቡ ሆኖ ይኖራል፡፡ እነዚህ የዘረፋ የሥራ ልምድ ያላቸው አለቆች ከሚያከናውኑት ሳሳ ያለ የቤተክርስቲያን አስተዳደር በተጨማሪ ዋና ሥራቸው አበጥ ያለ ካዝናና ደከም ያለ የሰበካ ጉባኤ ያለበትን ደብር እየፈለጉየከተማው ሀብታሞች እንኳ ለሚቀኑባቸው የማይቋረጥ ውስኪ አውራጅና ጮማ ቆራጭ ለሆኑ የሀገረ ስብከቱ ቋሚ ደላሎች ሪፖርት ማድረግ ነው፡፡ ከዚያም እየናረ ሄዶ እስከ ብር 500 ሺ በደረሰው የዝውውር ገብያ መጫረት ነው፡፡በዚህ መንገድ ከፍለው ዝውውር የፈጽሙና ከደሀ መቀነት የተገኘና የዕንባ ሚሊዮን ብሮችን ለማፈስ የታደሉ፣ የግፍ ሕንጻዎችን የገነቡ፣ የነሱ ሳያንስ ለውሻማዎቻቸው ሳይቀር ቅንጡ መኪናዎችን የገዙ የቤክርስቲያን አይጦች በስም መዘርዘር ባያስፈልግም አንተ ግን ከፈለክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ደላሎችን አንድ ውስኪ አውርደህ ማናዘዝ ነው፡፡የእነዚህ አለቆችና የአምስቱ ከለባት ዝውውር ፍጹም ሓላፊነትና ተጠያቂነት የጎደለው በመሆኑ ሁሉም ቃል ኪዳን የተገባቡ ይመስል ቋንቋቸው አንድ ነው፡፡ ትንሽ ጠንከር ያለ ሰበካ ጉባኤ ሲገጥማቸው… እኔ አባ እገሌ እንደሆንኩ አንዲት ሻንጣ ነች ያለችኝ እሷን አንጠልጥዬ መጓዝ ነው ይሉልሃላ! በዘረፋ የገዙትን መኪናውስ ቤቱንስ የት ረስተውት ይሆን? …ከዚያም አባታችን የዛሬ ዓመት ሂሳብ አልተዘጋም፣ ንብረት አልተቆጠረም፣ ሪፖርት አልተደረገም ሲባል…እኔ ከመጣሁ በኋላ እንጂ ከእኔ በፊት ያለውን አትጠይቁኝ በሚል የውሾን ነገር ያነሳ…አንድ ዓይነት ፈሊጥ የዝርፊያ አጋራቸውን ይከላከላሉ፡፡
ትላንት ትላንት ጴንጤው እንዴት ከኦርቶዶክስ ተቀየርክ? ሲባል ሰካራም በሆኑና ሥነ ምግባር በጎደላቸው አገልጋዮች ምክንያት ይሉ ነበር ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ለመንጋው በማይራሩ ሌቦችና ቀጣፊ አገልጋዮች እንደሚሆን እርግጥ ነው፡፡
ስለዚህ ሰበካ ጉባኤ፣ ምዕመናን፣ሰ/ት/ቤቶች የቤተክርስቲያን የሥራ ኃላፊዎች ሲዘዋወሩ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ባለው መልኩ እንዲሆን ድምጻችንን ማሰማት ያለብን ከመሆኑ ባሻገር፤ አለቆች ወይም አምስቱ ከለባት መልካም ሲሰሩ ደረጃቸው ከፍ የሚልብት፣ ሲማስኑ ደግሞ ከደረጃ ዝቅ ብለው የሚያገለግሉበት አሠራር መዘርጋት በጣም አስፈላጊና ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ርእስ ለይቶ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን እንደማሳያ ማንሳት ያስፈለገው የአዲስ አበባው አስተዳደር መስተካከል ለየሀገረ ስብከቱ መስተካከልወሳኝ በመሆኑ ነው፡፡
በዚህ በእኛ ዘመን…በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ተዘግተዋል፣ተቃጥለዋል፣ፈራርሰዋል፤ በተዳከመ የቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ምክንያት ብዙዎች በሰማዕትነት ታርደዋል፣ ከእነ ሕይወታቸው ተቃጥለዋል፤ እርስ በእርሳችን በዘውግ፣ በጥቅም ተለያይተናል፣ በሦስት ፓትርያርኮች ለመመራት እየተውተረተርን ከመሆኑ በላይ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን ጥላሸት ለመቀባት የሚደረገውን ርብርብና ከፋፍሎ ለመግዛት በፖለቲከኞች በየጊዜው የሚሸረቡትን ሴራዎች ደምረንበት፤መረን የለቀቀውን ይሄንን አስተዳደራዊ ልሽቀት በጊዜ ማረም ካልቻልን ጸጸታችን መመለሻ የሌለው ይሆናል፡፡ ለቤተ ክርስቲያንና ለኢትዮጵያ ትንሣኤ ከባለ ሥልጣን እስከ ተራ የመንደር ዱርዬ በብዙ ማስፈራሪያና ዛቻ ተከበው ቀን ከሌሊት ሁሉ ነገራቸው ለሆነችው እናት ቤተክርስቲያናችን ለሚተጉ እነ መ/ር ዘመድኩን የመሰሉ ትጉህ የቤተክርስቲያን ልጆች እንቅስቃሴና ልፋት ከባድና አድካሚ የሚያደርገው ቤተክርስቲያን እየተመራች ያለችው ለመንጋው በማይራሩ፣ጨካኝ፣ ራስ ወዳድ፣ ሙዳየ ምጽዋት ገልባጮና መሸተኞች በሆኑ አምስቱ ከለባት መሆኑ ነው፡፡ የዚህ የጡመራ መድረክ አባላት ዓላማ የቅድስት ቤተክርስቲያን ልጆች ከእኩይ ተግባራቸው ተመልሰው ለኢትዮጵያና ለቤተክርስቲያን ትንሣኤ በጋራ እንድንሠራ የማንቃት ሥራ ለመሥራት እንጂ ማንንም ለማሳጣት ወይም ለማሸማመቅ ባለመሆኑ እግዚአብሔር አመላክ ለእነዚህ የእናት ጡት ነካሾች ልብ ይስጥልን እንላለን!!!
በዚህ በጾመ ፍልሰታ እግዚአብሔር አምላካችን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ከእነዚህ የእናት ጡት ነካሾች ቤተክርስቲያናችንን ነጻ እንዲያወጣልን በጸሎት እንጠይቅ፡፡
በሚቀጥለው ክፍል
ዘረኝነትና ማኅበራት(በውኑ ማኅበራት ከዘረኝነት የጸዱ ናቸው?) የሚለውን እንመለከታለን
ይቆየን!

