በጩኸት፣በደባና በቡድንተኝነት ውሸት እውነት ሊሆን አይችልም!

መቼም ቤተ ክርስቲያን ያልወለደችው የለም! የዲጄው አሉላን ዓይነት አካይስትና ልቡሰ ሥጋ አጋንንት፣ እንደ ቅዱስ ዲዮስቆሪዮስ ከእውነትና ከእውነት ጋር ብቻ ወገንተኛ የሆኑ አቡነ ሩፋኤልን ዓይነት ቅን ልብ ያላቸው እውነተኛ አባቶች፣  እንደነ ‹‹ቀሲስ›› በላይ ጸጋዬን ዓይነት ዕውራነ ልብም ጉዳትን የሚጸንሱ፣ በደልንም የሚወልዱ ሆዳቸው ተንኮልን በማዘጋጀት የተካኑ በዚሁ ብቻ የሚኖሩትን አፍርታለች፡፡ቤተክርስቲያን የአደባባይ ብቻ ሁኖ የቀረው  ልቅሶአችንን ስትመለከት፣ በዚህ የቤተክርስቲያ የመከራ፣ የስደትና የሰማዕታት ዘመን እንኳ ሴረኞች ውስጥ ለውስጥ ሴራቸውን መቀጠላቸውን፤ ነጋዴዎችም ትርፍ በትርፍ መሆናቸውን፤ በአደባባይ ብቻ ለዓለም ሙተናል  ብለው የሚሰብኩን አባቶች የገዛ ወንድቸውን ለፍቅረ ሲመት ሲሉ ሸጠው በሹመት መንበሽበሻቸውን ስትመለከት ምን ትል ይሆን??? አሁን አሁን ኦርቶዶክሳውያን ለፍቶ አዳሪ እውነት ተናጋሪ መሆናችን ቀርቶ መስሎ አዳሪዎች ሁነን መኖሩ ሰምሮልናል፡፡ ይገርማችኋል ዛሬ አንድ ወዳጄን አግኝቼው ምን ባክህ የሲኖዶሳችን ስብሰባ እኮ አሁንም ልክ እንደ ድሮው ማንን እንሹም? ማንን እንሻር? ማንን ከሀገረ ስብከቱ እናፈናቅል?…ሁኖ እንደ ቀጠለ ነው አይደል? ብዬ በጨዋታ መካከል አነሳሁለት፡፡እንዴ የቅዱስ ሲኖዶስ ስበሰባ እኮ ተቋርጣል!ሐራ ላይ አላነበብክም እንዴ? እረ እነ እገሌም እነ እገሊትም… ፖስት አድርገውታል! አለኝ፡፡ እኔም በጣም የማከብረው ትልቅ ወዳጄ ስለሆነ ሰሞኑንም በሥራ ጫና ምክንያት ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ ስላልጎበኘሁ እንዴ እውነት ተቋርጦ ይሆን እንዴ? ብዬ ጥርጣሬ ገባኝ፡፡ ከአሁን ከአሁን ተለያይተን ባረጋገጥኩ ብዬ ስመኝ ተለያየንና ምሳ ሰዓት ስለነበር አንድ የቅርብ ወዳጄ የሆኑ ብጹዕ አባት ጋር ስደውል…ወዲያው ነገሩ ገብቶአቸው ኖሮ አይ የእኔ ልጅ በቃ ሐራ ትጫወትባችኋለች አይደል? እረ እንደዚህ የሚባል ውሳኔ ከየት መጣ አሉኝ? በምጸት ንግግር፡፡

ከሁሉ የገረመኝ ዛሬ ይህን ጹሑፍ እስከጻፍኩበት ጥቅምት 20 ቀን 2012 ዓ.ም ሌላውን በሀሰትና መረጃና በተሳሳተ ዜና ሲኮንኑ የሚውሉት የሀሰት መረጃውን ያስተላለፉት አንዳቸውም ይቅርታ አሳስተናችኋል የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ እንደ ቀጠለ ነው አለማለታቸውን አስገርሞኛል፡፡በርግጥ ዲጄው አይፈረድበትም የጫጉላ ጊዜውን ስላልጨረሰ ይሆናል ብዬ ባስብም ወሬ አራጋቢዎቹ ግን ይቅርታ ባለመጠየቃችሁ እጅግ አፍሬባችኋለሁ፡፡

እኔም ደግሞ የተዘናጋሁት አንድ የዲጄው አሉላ ወዳጅ በቃ አሁን ላገባ ነው ሐራ ላይ አልጽፍም ብሎ መማል መገዘቱ አስረግጦ በነገረኝ ተዘናግቼ ነው!ለካ ድመት መንኩሳ….ነው ጉዳዩ! ስለ ዲጄው ካነሳሁ አይቀር ይገርማችኋል ቀኑ እሁድ ከቅዳሴ መልስ ነው መስከረም 25 ቀን 2012 ዓ.ም! አንዱ ወዳጄ ደወለልኛና ሽማግሌው፣ ወታደሩና ዲጄው እኮ ‹‹ለመንገደኛው ሁሉ ተክሊል በማደል ላይ ያለችው ቸርች›› ለእርሱም አሻረችው አለኝ፡፡ ለጥቂት ጊዜ ግር አለኝ፡፡ ቀጠለ እድሜ ለማኅበሩ ሽማግሌው(አንዳንዶች ዕድሜውን ከሃምሳ ሲያዘልሉት ሌሎች አይጠቅመውም ይላሉ) የታናሽ ታናሽ…ታናሹ ከምትሆን በሃያዎቹ መጀመሪያ ላይ ካለችው ወጣት ጋር መጋባቱን ፎቶ ላከለኝ፡፡ እኔም ጎሽ ቤተክርስቲያን ከአሉላ ዓይነት ብር አምላኩ እፎይ ልትል ነው ብዬ ደስ አለኝ፡፡ ትዳር ደጉ ስንቱን ገርቷልና ነው፡፡መቼም መንፈስ ቅዱስ ፊት ጸፍቶ አፍ ከፍቶ ያናግራል እንዲሉ የመርሐ ግብር መሪው መ/ር አስቻለው ከበደ እስከ ዛሬ አላምንም ብትሉም ቅዱሳን ፓትርያርኮችን፣ ብጹአን አባቶችን፣ አበው መነኮሳትን በአጠቃላይ ቤተክርስቲያኒቱን በአደንዛዥ ዕፅ እና በሲጋራ በተጨማለቁ ጣቶቹና አንደበቱ ያለ ማንም ከልካይ ሲሰድብ፣ሲያዋርድ ማሳቂያና መሳለቂያ ሲያደርገን የነበረውን ሰው ቤተክርስቲያን አክብራ(አንግሳ) የክብር ዙፋን ላይ እንዳስቀመጠችው አረጋገጠልን፡፡ልብ ያለው ልብ ይበል!!!

እዚህ ላይ ሌላው ትኩረቴን የሳበው ጉዳይ ደግሞ ሠርጉን ተከትሎ ያለስሙ ስም ሰጥተው በተሳዳቢነቱ ሊገስጹት ሲገባ ነገ የስድብ ውርጅብኝ ፍራቻ በሚመስል መልኩ በጥንቃቄ መመርመር የሚገባቸው ሙገሳ ሲያቀርቡ የዋሉትን ሰዎች ጉዳይ ነው፡፡ በመሠረቱ ጥቂት ጥገኛና አድርባይ ያልሆኑ ወንድሞችና እህቶች በስተቀር ሌሎች በአብዛኛው ፌስ ቡካቸው ላይ ሰውን ታጠቅ ታጋል ቤተክርስቲያንህን ጠብቅ የሚሉ በተግባር ግን ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት ከተሰለፉ የፌስ ቡክ አርበኞች ብፁዓን አባቶችን የሀገረ ስብከታቸውን ጭምር ስም በመጠቀም ጥል ከሚዘሩ በርካቶች በአደባባይ መምህር ወመገስጽ ዘኢያደሉ ለገጽ ነን! የሚሉ በተግባር ግን ቤተ ክህነት ግቢ ውስጥ የሚልከሰከሱ ውሾችን ከመከተል መቆጠብ አለብን፡፡

ከዚህ በኋላ ሐራውያንና በድብቅ ሦስት ወይም አራት አካውንት ከፍተው የሚንቀሳቀሱ ታዋቂ ነገር ግን የምዕመናን ሕይወት ቀጣፊ ሰባክያንን እንዴት እንደሚጫወቱብን በተከታታይ እንመልከታለን፡፡

ለአሁኑ ግን ቅድም እንደነገርኳችሁ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ረቡዕ ጥቅምት 12 ቀን 2012 የቀጠለ ሲሆን እስከ ዛሬ ድረስ ከዘጠኝ አጀንዳዎች በላይ ተመልክቷል፡፡ የዘንድሮውን ስብሰባ እንደድሮው ለመዘገብ የተቸገረው ዲጄው አሉላ ጥቅምት 13 ቀን ሰበር ዜና፡ቅ/ሲኖዶስ ስበሰባውን ሊያቋርጥ ነው ብሎ ከዘገበ በኋላ በ15 እና በ16 የአይነኬ አካላት አጀንዳ በመታየቱ ምክንያት ለመዘገብ ቢቸገርም እንደ ተለመደው ዛሬ ጥቅምት 20 ቀን 2012 ዓ.ም አቡነ ያዕቆብ ላይ አጣሪ ሆነው ከተመደቡት አንድ ‹‹ብፁዕ›› አባት በወንድማቸው ላይ በሠሩት አኩሪ ተግባር ያገኙትን ሹመትና ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ ከደቡብ አፍሪካ ሀገረ ስብከት ተነሱ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ተመደቡ! ብሎ አስነብቦናል፡፡

ሐራውያን እኩያንና የዲያብሎስ የግብር ልጅ ፍቅረ ነዋይ ወዳጅነታቸውን ለማረጋገጥ እስቲ ሰለ ሴራቸውና ለምን አቡኑን የማሳደድና ስማቸውን የማጠልሸት ተግባር ላይ ተጠመዱ የሚሉትን እናንሳ፡፡

ከጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ቅዱሳንና ብጹዓን አባቶች ያላሉትንና ያልወሰኑትን የአቡሃ ለሐሰት ልጆች ናቸውና ፈብርከው እውነተኞቹንና ብርቱ ተጋዮቹን እነ ዲ/ን ዓባይነህ ካሴን ጭምር ብዙዎች በየፌስ ቡኩ ሲቀባበለው ተሳስተን አሳሳትናችሁ እንኳን አላሉንም፡፡

ከዚህ በፊት እንደነገርኳችሁ ሐራውያንና መስሎ አዳሪ እስስት ሰባክያን ሁሉም ሰው ወርሃዊ ተቀላቢ ይመስል ዘወትር ቢሄድ በማያጣቸው በአምስት ኪሎው ውስኪ ቤት እና በአራ ኪሎዎቹ ካፌዎችና ሬስቶራንቶች ቃለ ጉባኤ ተይዞ ይጻፍበት አይጻፍበት ተብሎ ይወሰንብሃል ወይም ይወሰንልሃል፡፡በቃ የእነዚህ እፉኝቶት ተግባር ይሄው ነው፡፡ ይገርማችኋል ከቅ/ሲኖዶስ አጀንዳዎች አንዱ የኢየሩሳሌም ሀገረ ስብከት ነበር፡፡ እናላችሁ ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም ስብሰባው ላይ ባልተገኙበት ሁኔታ ከአንድ ቀን ተኩል በላይ  ቅ/ሲኖዶሱ በሸዋና በትግሬ ጳጳሳት መካከል የከረረ ጭቅጭቅ ውይይት አድርጎ መሸናነፍ ስላልቻለ(የጎጥ ጉዳይ መቼም ከባድ አይደል!) ከዚያ ሁሉ ውይይት በኋላ አስተዋይ በሆኑ ብፁዓን አባቶች አስታራቂነት እኔ ለማንሳት የማልፈልገው ያ ሁሉ ውንጀላና ክስ ብሎም አንዳንዱ ውግዘት የሚያስፈልገው ጉዳይ በሁለቱም በኩል በቃ በቃ ሊቀ ጳጳሱና አምስቱ መነኮሳት ይታረቁ ተብሎ እጅግ ወደ አስፈሪ ደረጃ ሊደርስ የነበረው ውይይት ተቋጨ፡፡ ሐራ ዘገበችው? እረ በጭራሽ!አፌን በዳቦ ብላ እልፍ! ለምን የኢየሩሳሌሙን አጀንዳ ደብቆ በማስቀረት ላለመዘገብ ተፈለገ? ብሎ አለመጠየቅ መንጋነት ነው፡፡ በእኔ እምነት ሊቀ ጳጳሱ በሌሉበት ሊቀ ጳጳሱን ሁነው የተሰይመው አንዱ ቡድን የሸዋ ስለነበር ሐራ ደግሞ ሸዋና እንትን መናፍቅ፣ ተሐድሶ፣ሙዳየ ምጽዋት ገልባጭ ቢሆን ምን ግዳቸው፡፡ አይነኬ ናቸው! እንደ ድመት እንትን ይሸፋፈንልሃል፡፡ ዛሬ ደግሞ እኚሁ ከጳጳሳት የማንም ቡድንተኛ ያልሆኑት የፈረደባቸው ሊቀ ጳጳስ ክቡር ዶክተር አቡነ ያዕቆብ አጀንዳ ይታይ ስለነበር ልብ ብላችሁ ካስተዋላችሁ ብፁዕነታቸው መልስ ሰጥተው የተወሰነው ከሰዓት 9፡00 ገደማ ነው፡፡ ሐራውያን የደቡብ አፍሪቃን ቤተክርስቲያን እንደ ቅርጫ ለመከፋፈል ላሰፈሰፉት የቤተክህነቱ አይጦች ጋር ቀሪ ያልተወራረደ ሂሳብ ስላላቸው አሁን ልገልጠው በማልፈልገው ሰው በኩል የአባቶችን እያንዳንዱን ንግግር በቀጥታ ስለሚከታተሉ ሳያስተውሉት አባቶች ገና ከስብሰባ ሳይወጡ 10፡00 አከባቢ ነው የለቀቁት፡፡

ይታይሃል ቤተክርስቲያን በእነማን እጅ እንደወደቀች? ሐራውያን ለምን በአቡነ ያዕቆብን ብቻ ለይተው ለማሳደድ ፈለጉ የሚለውንና በሁለተኛው ዙር አጣሪ ሆነው የሄዱት አካላት ምን ምን ተግባራትን ፈጽመው፤እነማንን አግኝተው ተመለሱ፣ የአጣሪዎቹን ግለ ታሪክ በማስረጃ አስደግፌ እስከማቀርብ ድረስ ብዙ በጥልቀት መግባት አልፈልግም፡፡ ነገር ግን ከአጣሪዎቹ መካከል የገዛ ወንድማቸውን ያው ከዚህ በፊት እንደሰማችሁት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ጠባቂ ለመሆን ካላቸው ከፍተኛ ጉጉት የተነሳ ውስጥ ለውስጥ 50 እና 100 ብር ከግንቦቱ ስብሰባ በፊት ለቀን ተማሪዎች በመስጠት መከራቸውን ሲያዩ መቆየታቸው ፀሐይ የሞቀው ሀገር ያወቀው ጉዳይ ነበር፡፡ ይህን ጥማታቸውን የተረዱት ሴረኞች ወጥመዳቸው ውስጥ ካስገቧው በኋላ በመጀመሪያ ሴራ ላይ የተሳተፉ የብዙ ሴረኞች ስም ከሚጠፋ እነ ሙጬን 58 ገጽ ሪፖርት ወደ 9 ገጽ አሳጥሮ ማቅረብና ሴረኞችን ሸፍኖ አብረው በአንድ ት/ቤት የተማሩ፣ በአንድ ገበታ የተመገቡ ተከራካሪ ቡድን የላቸውም የተባሉትን ወንድማቸውን አንዱን ስለ ብዙዎች አሳልፎ የመስጠት ፈሪሳዊና ቤተክህነታዊ ጠባይ ቅድሥት ሥላሴ ኮሌጅም እያሉ የሚታወቁበትና የኖሩበት በመሆኑ ምናልባት ነገ ብዙ መከራ የሚቀበሉበትን የኮሌጅ የበላይ ጠባቂነት ተሸለሙ ማለት ነው፡፡ ይሄ ካልተሳካ ደግሞ በትክክል ከደቡብ አፍሪቃውያኑ ቄሶች በነበረኝ የስልክ ምልልስ ማረጋገጥ እንደቻልኩት እኒህ ሊቀ ጳጳስ ይመደቡልን ዓይነት ሀሳብ ዙሪያ ሲሽከረከሩ መክረማቸውን ለመረዳት ችያለሁ፡፡

ለመሆኑ ሊቀ ጳጳስ ክቡር ዶክተር አቡነ ያዕቆብ ሐራውያን እንደሚስሏቸው ናቸውን? ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች የሰበሰብኩትን እነሆ

  • ብፁዕነታቸው በምንም መንገድ ክፉ  ያደረገባቸውን እንኳ አንድ ቀን በአደባባይ በክፉ የማያነሱ፣ የሌላውን በደል የራሳቸው አድርገው የሚሸከሙ፤
  • በጸሎታቸው በኢትዮጵያ በመላው አፍሪካ በርካቶች ከሰይጣን እስራት የፈቱ፣ልጅ ላልነበራቸው ለበርካቶች ልጅ እንዲወልዱ ምክንያት የሆኑ፣ በተግባር ዕውራን የነበሩትን ያበሩ፣ሽባ የተረተሩ በአጠቃላይ ጥቂት አሉን ከምንላቸው የጸሎትና የፈውስ አባቶች መካከል አንዱ መሆናቸውን ኢትዮጵያ፣ኬንያ፣ደቡብ አፍሪቃ…ያሉ ማንም ሰው ቢጠይቅ ለዚህ ሕያው ምስክር የሆኑ በርካታ ሺህዎችን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል፤
  • በስም ሳይሆን በተግባር በተፈተነ መልኩ በተለይ በእንግሊዘኛ ቋንቋ በማስተማር፣ በመግባባትና በመሥራት ያሉና ከሚችሉ ከጥቂት አባቶች መካከል የሆኑ፤
  • በዘር፣በወንዝ፣በጎጥ ጨርሰው የማያምኑ በዚህ የማይታሙ ፍጹም በብትሕውና ሕይወታቸውን የሚገፉ፤
  • ለራሳቸው የተለየ የክብር ቦታና ከበሬታ እንዲሰጣቸው የማይፈልጉ፣ ሁሉንም እንደየ አቅሙ ተሸክመው ከሕጻናት ጋር እንደ ሕጻን፣ ከአዋቂዎችም ጋር እንደአዋቂ ሆነው ብቻ ሰው እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ ሆኖ ብቻ እንዲኖር እንጂ በአገልግሎት ዘመናቸው ሁሉ ለማንም ሸክም ያልሆኑ፣ ከምዕመናን ጥቅም ሰብሳቢና ፈላጊ ያልሆኑ ቤተ ክርስቲያኑቲ በምትሰጣቸው ደሞዝ ብቻ ለመኖር የሚሞክሩ፣ በልተው የማያስበሉ ምንም አይነት ከቤተክርስቲያን ገንዘብ የመንካት አባዜ የሌለባቸውና በዚህ ማንም ምንም ማስረጃ ማቅረብ የማይችል መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን

ከ Divinity College International መስከረም 24 ቀን 2012 ዓ.ም  በአመራር፣ በአስተዳደርና በስነ መለኮት የክብር ዶክትሬት( Honorary Doctrate) አበርክቶላቸዋል፡፡ከዩኒቨርስው ምንጮች ለመረዳት እንደቻልነው ከበርካታ ተወዳዳሪዎች መካከል ለክብር ዶክትሬቱ ያበቃቸው በሚመሯቸው አህጉረ ስብከቶች በማኅበረሰብ ልማት፣ ወጣት መሪዎችን በማፍራትና በማሳደግ ባበረከቱት አመርቂ የእግዚአብሔር ሥራ፤በማኅበረሰቡ ውስጥ ባበረከቱት አብሮና ተከባብሮ የመኖርና የሀገር ግንባታ ሥራ፣ አንጻባራቂ የሆነ የክርስትና እምነትን የማስፋፋት ተግባር፤ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን እምነት የማስተዋወቅና የማስፋፋት ሥራ እና በመላው አፍሪካ አብያተክርስቲያናት ሕብረት(AACC) በምክትል ፕሬዝዳትነት ባበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ምክንያት መሆኑን ነው፡፡

አሁን የሄዱት አጣሪዎች የእነ ሙጬን ሪፖርት ከ58 ገጽ ወደ 9 የመከመለስ ሥራ ከመስራታቸው በሻገር ከዚህ በፊት በእነ መጋቤ ሃይማኖት ቆሞስ አባ ጥዑመ ልሳን አዳነ ዘመን የተባረሩ የቀድሞ የሰበካ ጉባኤ አባላትን የእነ ገዛኸኝ አበበን በደቡብ አፍሪካ የእነ ማዘር ካባን ሪፖርት ብቻ በማቅረብ በደቡብ አፍሪቃ ያሉት ካህናት ነጋዴዎችና አገልግሎት በአግባቡ እንደማይሰጡ፣ቤተ ክህነቱ ለበርካታ ጊዜያት ለክስ ያመቸው ዘንድ መዋቅሩን የማፈራረስ ሥራ ማለት ሐራ እንዳለችው ለሦስት ጊዜያት ብቻ ሳይሆን ለበርካታ ጊዜያት የሚጠይቁትን ባለመፈጸም ያለ ሊቀ ጳጳስ ሁለት ወይም ሦስት ዓመት እንዲቆይ በማድረግ መዋቅሩን የማፈራረስ ሥራ ሠርተው ሲያበቁ የፈራረሰ መዋቅር ነው ያለው፤ አብያተ ክርስቲያናቱ አልተደራጁም፣ ሥራ አስኪያጁ ደካማ ነው፣ የደቡብ አፍሪካ ካህናትና ሰበካ ጉባኤ አባላት አንፈልጋቸውም ብለዋል ብሎ የምዕመናኑን የካህናቱን ትክክለኛ ምስክርነትና በተለይ አቡነ እንጦስ በአደባባይ ሰው በተሰበሰበበት ብፁዕነታቸው በደቡብ አፍሪካ ማንም ሊፍቀው የማይችል ትልቅ ታሪክ ነው የሰሩት! ብለው በአንደበታቸው የመሰከሩትን ገሸሽ አድርጎ ፍጹም ሐሰት የሞላበት ሪፖርት ማቅረብ ከጸሐፍት ፈሪሳውያን ክስ ተለይቶ የማይታይ ከመሆኑም በላይ እነዚህን ምዕመናን ከአባታቸው የመለየት ሥራ በመሥራታቸው ታሪክ ይፋረዳቸዋል! ተስፋሆሙ ለስዱዳን የሆነ መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ይዋጋቸዋል ብዬ አምናለሁ! በዚህ በውሸታቸውም ዋጋም ይከፍሉበታል ብዬ አምናለሁ፡፡

በመጨረሻም ብፁዕነታቸው ለቅዱስ ሲኖዶስ አበላት የተናገሯቸውን ንግግሮች አንስቼ ጽሑፌን ላጠናቅቅ፡፡

  • በመጀመሪያ ደረጃ ዕዳ በደሌንና ወንጀሌን ከ58 ገጽ ወደ 9 ገጽ ስላወረዳችሁልኝ እጅግ በጣም አመሰግናለሁ፡፡(በርካታ አባቶች ቅዱስነታቸውን ጨምሮ ፈገግ ያስባለ ንግግር)
  • መቼስ እኔ በዚህ ጉዳይ ማድረግ የነበረብኝ ዝም ማለት ነበር፡፡ ምክንያቱም ክርስቶስ እንኳ ሲሰቀል አልተናገረምና፡፡ እኔ ግን የእናንተ የአባቶቼ አእምሮ እንዳይቆሽሽ ብዬ ብቻ ነው የምናገረው ደቡብ አፍሪቃውያንን በተመለከተ ይሄው እኔው ራሴ በዙሉ ወይም በቆ(ጦ)ሳ ቋንቋ እንዲተረጎም ያደረኩት የ14ቱ የቅዳሴያት መጽሐፍ፣ይኸው በ2008 ዓ.ም ወደ እንግሊዘኛ ተተረጎሞ እንዲታተም ያደረኩት ውዳሴ ማርያም፣ ቀሲስ በቀለ እነ ሙጬ ስሜን አጥተዋል ይጠየቁልን ብለው ለቅዱስነታቸው ያስገቡትና ለእኔ ግልባጭ ያደረጉት የእነ ሙጬን ተንኮልና ሴራ የሚያጋልጥ ደብዳቤ(ከፍ እያደረጉ መጻሕፍቶቹንና ደብዳቤውን እያሳዩ)፤ ደቡብ አፍሪቃውያን የሚጠቀሙበትን አብያተ ክርስቲያናትን በተመለከተ 33 ያደረስኩ ሲሆን በተለይ አምስቱ ታላላቅ ካቴዴራሎችን ለደቡብ አፍሪካውያን የገነባሁ እኔው ነኝ፡፡ሳውዝ አፍሪቃ ስደርስ ኢትዮጵያውያን የሚገለገሉበት የነበረ አንድ ቤተክርስቲያን ብቻ ሲሆን ወደ ዘጠኝ የሚደርሱትን አብያተ ክርስቲያናትንና ከ20 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ በሚሆን ቦታ ላይ የካህናት ማሰልጠኛ ገዳም ገንብቼ ሁሉንም በግለሰብ ስም አሊያም በቦርድ ሳይሆን በኢ/ኦ/ተ/ቤ ስም እንዲመዘገቡ አድርጌአለሁ፡፡ ነገም እነዚህን አብያተ ክርስቲያናት በአግባቡ በጥንቃቄ የማስረክብ ሲሆን ለቅዱስ ሲኖዶስም ሪፖርት አቀርባለሁ፡፡ ከአራት ዓመት በፊት በሐሰት ክስ ከደቡብ አፍሪካ ተነስቼ ወደ ምስራቅ  አፍሪቃ ስላክ ከ30 ዓመት በላይ መንበረ ጵጵስና ያልነበረውን ኬንያ ግዙፍ መንበረ ጵጵስና ሠርቼ በግሌ ከተሸለምኩት ዘመናዊ መኪና ጋር አስረክቤአለሁ፡፡ በጅቡቲም በእነ አባ ዮናስ ዘመን የቅድስት ማርያምን ቤተክርስቲያን፤ በደቡብ ሱዳን ጁባም የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያንን አሠርቼ ያጠናቀቅኩ ሲሆን ከከፍተኛ ባለ ሥልጣናት መካከል አንዱ በጽኑ ደዌ ይሰቃይ የነበረ ወንድማችን ስለተፈወሰ በደስታ ወደ 4 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ሰጥቶን ተረክቤ ለምዕመናኑ አስረክቤአለሁ፡፡ በዛምቢያ፣በቦስትስዋና፣ በኢኳቶሪያል ጊኒ የተሰሩና በግንባታ ላይ ያሉትን ማየት ይቻላል፡፡አባቶች በተቻለ መጠን መለያየትን ከመዝራት፣ በሌላው ሀገረ ስብከት ጣልቃ ከመግባት ተቆጥበን እርስ በእርሳችን ተጋግዘንና ተደደጋግፈን ብንሰራ መልካም ይመስለኛል፡፡ከዚያ ውጪ ገና በጨለማው ዘመን ከዛሬ አራት ዓመት በሩዋንዳ ከኤርትራ የቅዱስ ገብርኤል ከኢትዮጵያ የመድኃኔዓለም ታቦት ይዘው ተለያይተው ይኖሩ የነበሩትን እግዚአብሔር ረድቶኝ በአንድነት እንዲያገለግሉ ማድረግ ችዬአለሁ፡፡
  • አባቶቼ አሁን የመደባችሁኝ ቦታ በርካታ የሌላ እምነት ተከታዮች ያሉበት ያልተደራጀ ቦታ ስለሆነ የምለምናችሁ በጸሎታችሁ እንድታግዙኝ ብቻ ነው፡፡አደራ አባቶቼ ቅድስት በሆነች ጸሎታችሁ አግዙኝ! ደቡብ አፍሪቃ ላይ ከአንድ ቤተ ክርስቲያን አሁን ወዳለበት እንዲደርስ የረዳኝ እግዚአብሔር ይረዳኛል ብዬ አምናለሁ፡፡
  • ቅዱስ አባታችን አቡነ ማትያስ ስላደረጉልኝ በጎ ነገር ሁሉ እጅግ አመሰግንዎታለሁ፡፡

በማለት ለእሳቸው ተብሎ የተፈጠረውን እስካሁን በስም የማናውቀውን ሀገረ ስብከት ማለቴ ነው ሩቅ ምሥራቅ ሀገረ ስብከት ፍጹም ትህትናና ታዛዥነት በተሞላበት መንገድ ምንም ሳያንገራግሩ ተቀብለው መውጣታቸውን አንድ ወዳጄ የሆኑ ሊቀ ጳጳስ ሌላው ቢሆን ስንት ግርግርና ጭቅጭቅ ነበረብን ብለው በአድናቆት አጫውተውኛል፡፡ለነገሩ በጩኸት በደባና በቡድንተኝነት ውሸት እውነት ሊሆን አይችልም! የበለጠ ደግሞ ነገ እውነታዎቹ ፍንትው እያሉ መውጣታቸው አይቀርም፡፡

የሆነ ሆኖ አሁንም ምንም እንኳን የተመደቡት አባት መልካም አባት ቢሆኑም በአሕዛብና በመናፍቃን ፈረጀ ብዙ ፈተናና ችግር ያለበትን የከንባታ ሀዲያ ሊቀ ጳጳስ ሀገረ ስብከታቸውን እንደያዙ በሪፖርት አቅራቢዎቹና በሐራ ተዋሕዶ መሠረት ፈረጀ ብዙ ችግር ወደ አለበት መመደባቸው ለደቡብ አፍሪቃ ምዕመናን ይጠቅም ይሆን? ውጤታማስ ያደርጋቸው ይሆን? ደምጹን ያለአግበባብ የቀሙት የደቡብ አፍሪካ ምዕመንንና ካህናት  ምን ይላሉ? የሚሉትንና ሌሎችንም የሰዎች አስተያየትና ከማጣራቱ ሂደት ጋር ያሉ የድምጽ፣የምስልና የወረቀት መረጃና ማስረጃዎችን ይዤ እመለሳለሁ!

እስከዚያው ግን ለሁለቱም ብፁዓን አባቶቼ መልካምና ስኬታማ የአገልግሎት ዘመን እመኝላችኋለሁ፡፡አሜን፡፡

ሳምኬት ነኝ

ጥቅምት 20 ቀን 2012 ዓ.ም

Leave a comment