አልሰማችሁም እንዳይለን ምን እናድርግ?

እንዴት ከረማችሁልኝ ወዳጆቼ?

መቼም እንደምትረዱት እየገጠመን ያለው ችግር እንኳን ጽፈንና አውርተን አይደለም ጸጥ ብለን በተቀመጥንበትም የምናደምጠው ነገር ጆሮን ጭው የሚያደርግ ስለሆነ ሌላ ሸክምና ድካም ላለመጨመር ብለን ነበር እስካሁን ዝም ብለን የከረምነው፡፡ አሁን ግን በአንድ ጉዳይ ላይ ሀሳብን መግለጥ የሚያስፈልግ ስለመሰለን ይህችን ጽሑፍ ጻፍንላችሁ፡፡

ወዳጆቼ የጀመርነው ዘመቻ ጌዴዎን ገታ ያደረግነው በአንዳንድ ወዳጆቻችን ምክር መሠረት ለጊዜው ቢዘገይ መልካም መሆኑን ስለተመካከርን እንጂ ጅብ እንደነከሰው እንስሳ ከዚህ በፊት የነካካናቸው ጉዳዮችን ዘንግተን አይደለም:: እንዲያውም ይገርማችኋል ጽሑፎቹን ካነበቡ በኋላ የሚያውቁንም ይሁኑ የማያውቁን እውነተኛ የቅድስት ቤተክርስቲያን ልጆች ያደረሱንልን ሸከማቸው የከበዱንና አእምሮን ወጥረውና አስጨንቀው የሚይዙ በደንብ የደለቡ ማስረጃዎችና መረጃዎች አውጡን… ልቀቁን… እያሉ አጨናንቀውናል፡፡ ዳሩ ቦ ጊዜ…ነው፡፡

ለዛሬ በየጊዜው ከሚታወጁ ምህላዎች ጋር በተያያዘ አንድ ሁለት ጉዳዮች ውስጤን እየኮረኮሩ አላስቀምጥ ስላሉኝ ነው ለመጻፍ የተገደድኩት፡፡ መቼም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የታዘዘው የሦስት ቀን ምህላ ያልሰማ ክርስቲያን አይኖርም፣የወደፊቱን የማኅበረ ሥላሴዎቹ የሰባት ቀን የምህላ ጥሪ፣የጎንደር ፣የአክሱም …ችግራችን እስካልተፈታ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ እንዴት አሳለፍናቸው? ስለቀጣዮቹስ ምን እያሰብንነው?

በርግጥ አሁን ያለንበት ወቅት በማኅበርም ይሁን በግል ከልብ ሁነንና እርስ በእርስ ያሉን ልዩነቶችንና ጎራዎችን ወደ አንድነት በማምጣት ልንተጋበት የሚገባ ጊዜ ነው፡፡ ታዲያ ምህላዎቻችን ታላቁ ነቢይ ኢሳይያስ በምዕ 1፡ 15 ‹‹እጃችሁን ወደ እኔ ብትዘረጉ ዓይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ፤ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም ፤ እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል፡፡››እንዳለ ፍሬ አልባና መልስ የማያስገኙ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ ብዙዎቻችን በተለይ ቤተክህነቱ አከባቢ ቅርበት ያለን አካላትእ ንደምናውቀው ክብር፣ ሀብትና ሥልጣን እሽቅድድም ላይ ያሉ ጥቂት በቡድን የተደራጁ ኃያላንና ራሳቸውን የቤተክርስቲያኒቱ አድራጊ ፈጣሪ አድርገው የሾሙ ብጹአን አባቶችን (ብዙዎቻቸው በሌላ ሰው ስም ወይም አካውንት የሚጠቀሙ ቢሆንም) እነሱን ጨምሮ ምህላ በታወጀባቸው ጊዜያት እንኳ የብዙዎቻችን የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን አለመዘጋታቸውን፣ ሃያ አራት ሰዓት ሊባል በሚችል ሁኔታ መስመር ላይ(online) መሆናችንና ከገንቢ ጽሑፍ ይልቅ አፍራሽ፤ ከማጽናናት ይልቅ በኀዘን ላይ ኃዘን የሚጨምር፣ ከሰላም ይልቅ ጥልና መለያየትን የሚሰብክ መሆኑን ስመለከት ለመሆኑ ቅዱስ ያሬድ ‹‹…እጅ ይጹም…›› ያለው የፌስቡክ እና የድኅረ ገጽ ተጠቃሚዎችን አይመለከትም እንዴ? ብዬ እንድጠይቅ አድርጎኛል፡፡

በእኔ እምነት እንደነዚህ ዓይነት ግብ ተኮር የሆኑ ምህላዎች ሲታዘዙ ኅሊናችንን በመግዛት አእምሮንና ጊዜን ከሚቆጣጠሩ የማኅበራዊ ሚዲያዎችና የመገናኛ ብዙኃን ማደንዘዣ ወሬዎች ካልተራቀ ብሎም ደግሞ ለእነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ይውል የነበረውን ገንዘብ መመጽወት እና ብዙውን ጊዜያችንን ከተንቀሳቃስ ስልኮቻችን ይልቅ የጸሎት መጽሐፍ የምንይዝበት ማድረግ ካልቻልን ምህላዎቻችን ፍሬ የሚያፈሩ ምላሽ የሚያስገኙ አይመስለኝም!!! ስለዚህ ከማኅበራዊ ሚዲያና መገናኛ ብዙኃን የድንዛዜ መንፈስ ወጥተን ለመለያየት በር የሚከፍቱ ወሬ አራጋቢነትን ተጸይፈን እውነተኛ የምህላ ሰዎች ልንሆን ይገባል እላለሁ፡፡

እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚገባን ነገር መቶ ቀን የተማርነው የዓውደ ምህረት ትምህርት አሊያም በየወሩ በየአውደ ምህረቱ የሚዘጋጁት የሦስት ቀንና የአራት ቀን ልዩጉባኤያት ፍሬ አልባ ሁነው በአንድ መስመር የማህበራዊ ሚዲያ ጽሑፍ የምንረበሽ፣ መረጋጋት የሌለን፣ ፈሪና ወኔ አልባ እየሆንን መምጣታችንን ስመለከት ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያ አንዱ የኦርቶዶክሳውያን ወኔ ሰላቢ ሆኖ አግኝቼዋለሁና ማኅበራዊ ሚዲያም ይሁን የመገኛ ብዙኃንን እንዴትና መቼ መጠቀም እንዳለብን መወሰኑ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ከዚህ በተጨማሪ በዚህ ዙሪያ ጥናቶች ተሠርተው ኅብረተሰባችን ከተያዘበት ባርነት ነጻ የማውጣት ሥራ፣ ተደጋጋሚ ውይይቶችና ምክክሮች ማድረግ ይገባናል፡፡

ሁለተኛው ጉዳይ በራሳችን ዜጎች በኢትዮጵያውያን እየደረሰብን ያለው ወረራና ዓይን ያወጣ ቤተክርስቲያንንና ኦርቶዶክሳውያንን ጠል ዘመቻና ሰይጣናዊ ተግባር ስልታዊ እና ውጤት ተኮር በሆነ መልኩ ልንዋጋው የሚገባን መሆኑ እንዳለ ሆኖ ሌላ ዘመቻ የሚያስፈልገው ጉዳይ አለ፡፡ ይኸውም በመካከላችን ያሉ ልዩነቶችና ደካማ የቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር መኖር ነው፡፡ መቼም ይህን ጉዳይ ሳነሳ ቅር የምትሰኙ ጥቅመኞች እንዳላችሁ ቢገባኝም እነዚህ ጉዳዮች ማንሳት ችግሮቻችንን ለመፍታት መነሻ ሰለሚሆን ማንሳቱ የግድ ነው፡፡

በመካከላችን ያሉ ልዩነቶችን መዘርዘሩ ለቀባሪ አረዱት ስለሚሆንብኝ ብዙም ለማለት አልፈልግም፡፡ ይሄ ደግሞ 365 ቀን ምህላ ብንይዝም እንዳንሰማ ያደርገናል ብዬ አምናለሁ፡፡እኔ ግን ተፈትቶ ባየው ደስ የሚለኝ በብጹአን አባቶቼ ውስጥ የማየው ዘርን፣ ወንዝንና ጥቅምን መሠረት ያደረገ ቡድንተኝነት ነው፡፡ በርግጥ ለዚሁ የተሰለፉ ማኅበራዊ ገጾች ልክ የጥቅምት 2012 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ተቋረጠ፣ አይቀጥልም…ምናምን እያሉ ሰው ግራ የሚያጋቡ፤ የበሬ ወለደ ወሬ በማመላለስ ብቻ በሚያገኙት ብር እቁብ የሚጥሉ፤ ሁልጊዜ የሲኖዶስ ስብሰባ በመጣ ቁጥር አጀንዳ የሚፈበርኩ የጨለማው ሲኖዶስ ቡድን አባላት በቃችሁ ማለታችን እንዳለ ሁኖ ማለት ነው፡፡

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ በቅድስት ቤተክርስቲያን አባቶች፣ ሰባክያን፣ ዘማርያንና ማኅበራት መካከል ያሉ ልዩነቶች በሀገራችን ተዋሐዱ እየተባሉ እየተለመኑ ያሉ 107 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አለ ብዬ አላስብም፡፡ ይህ ልዩነት የበለጠ እንዲሰፋ ደግሞ ቀን ከሌሊት ለእኩይ ተግባር የሚተጉ ራሳቸውን የቤተክርስቲያኒቱ የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊዎች አድርገው የሾሙ ጥቂት ጥቅመኛ የቤተክርስቲያን መዥገሮች አሉ፡፡ በጣም የሚገርማችሁ ከጥቂት ጊዜ ወዲህ የቅዱስ ፓትርያርኩንና የብጹአን አባቶችን የዕንባ ጎርፍ በማየት አምላካችን በእነሱ ዕንባ ሊታረቀን ነው ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ወዲያው ደግሞ ሀገረ ስብከት ለመቀማማት፣ወደ ከተማ አሊያም ወደ ውጪ አህጉረ ስብከት ለመመደብ በብጹአን አባቶች መካከል የሚደረገውን ፍትጊያና መገፋፋት፣የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ጠባቂ፣ዲን …ማናምን ለመሆን የሚሸረበውን ሴራ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን የፍቅረ ነዋይ አምሮት መወጫ ለማድረግ የሚደረገውን ትርምስ፣ የሲኖዶስ ስብሰባ በመጣ ቁጥር ‹‹ታዋቂ›› ሰባክያንና ግለሰቦች በብጹአን አባቶች ማረፊያ ሲርመሰመሱ ስመለከት ቀደሞ በአባቶች ዕንባ መነሻነት የጨበጥኩት የመሰለኝ ተስፋ መልሶ እንደጉም ተኖ ይጠፋል፡፡ በሌላ በኩል ይህ አደረጃጀት፣ ቅንጅትና ስምሪት ምነው ለወንጌል አገልግሎት ቢጠቀሙበት ብዬ መቆጨቴ አልቀረም፡፡ በርግጥ በአባቶቻችን መካከል የምናያቸው ልዩነቶች ነቢዩ ሰሎሞን በምሳ16፡28‹‹ ጠማማ ሰው ጥልን ይዘራል፤ ጆሮ ጠቢ ሰው የተማመኑትን ወዳጆች ይለያያል፡፡››እንዲል የአባቶቻችን መለያየትና ቡድንተኝነት ምክንያት አንገተ ደንዳኖች፣ልቦናቸውና ጆሮአቸው ያልተገረዘ ጠማማና ጆሮ ጠቢሰ ዎች በአባቶች ዙሪያ መኮልኮላቸው ነው፡፡ ስለዚህ አባቶቻችንን የእነዚህ ጠማማና ጆሮ ጠቢ ኢ-ክርስቲያናዊ ማንነት የተላበሱ ሰዎችን ማንነት በማጋለጥ ልንረዳቸው ይገባል፡፡ በዚህም መንገድ አባቶቻችን አንድ ከሆኑ የቤተክርስቲያንና የሀገር አንድነትና ሰላም ይመለሳል፡፡ እኛም የማንም ጆቢራዎች ማላጋጫ አንሆንም ማለት ነው፡፡

የሰላምና የአንድነት አምላክ እግዚአብሔር ሰላሙንና ፍቅሩን ሰጥቶን ምህላችን በእርሱ ዘንድ የሚደመጥና መልስ የሚያመጣ እንዲሆን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን!

ሳምኬት ነኝ!

ተጻፈ ጥቅምት 17 ቀን 2012 ዓ.ም

Leave a comment